Search

ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ስኬት የሆነው አረንጓዴ ዐሻራ

ሓሙስ መጋቢት 24, 2018 119

ኢትዮጵያ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከጠቅላላ የቆዳ ስፋቷ 35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው በደን የተሸፈነ እንደነበር የታሪክ መዝገቦች ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ ለዘመናት በዘለቀው ቁጥጥር ያልተደረገበት የደን ጭፍጨፋ፣ ለግብርና ማስፋፊያ የሚደረግ ምንጣሮ እና ለማገዶ የሚውል የኃይል ፍላጎት መጨመር የሀገራችን የደን ሽፋን በአስፈሪ ሁኔታ እንዲመናመን አድርጎታል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 15.5 በመቶ ገደማ የነበረ ሲሆን፣ በየዓመቱም በአማካይ 92 ሺህ ሄክታር ደን ይወድም ነበር። ይህ የደን ሀብት መመናመን የውኃ አካላት መድረቅን፣ የአፈር መሸርሸርን እና ተደጋጋሚ ድርቅን በማስከተል ለምግብ ዋስትና መታወክ እና ለኢኮኖሚ መዳከም ዋና ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

ሳይንሳዊ መርህ እና ስልታዊ አመራር

በመጋቢት 2010 . የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የሀገር ሕልውና እና የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት 2011 . የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በይፋ ተጀምሯል። መርሐ ግብሩ በዘልማድ የሚከናወን ሳይሆን፣ የችግኝ ዓይነቶች ከየአካባቢው የሥነ-ምህዳር (Agro-ecology) ሁኔታ ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ፣ የጽድቀት መጠናቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጭምር የሚከታተል ሳይንሳዊ ሂደትን መሠረት በማድረግ ነው።

መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ የችግኝ ተከላ ቁጥሩን 54 ቢሊዮን ለማድረስ ያለመ ታላቅ ግብ ተቀምጦ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። ይህ መርሐ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ታይቶ የማይታወቅ ሕዝባዊ ንቅናቄን የፈጠረ ሲሆን፣ በአንድ ጀምበር ብቻ 700 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ መቻሉ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ቁርጠኝነት ለዓለም ያስመሰከረ ክስተት ሆኗል።

የመረጃና አኃዞች ምስክርነት

2009 . 15.5 በመቶ የነበረው የሀገራችን የደን ሽፋን በአሁኑ ወቅት ወደ 23.6 በመቶ ከፍ ብሏል። በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ (UNFCCC) መመዘኛዎች መሠረት የተረጋገጠው ይህ 6.4 በመቶ ዕድገት የሀገራችንን የደን ሽፋን በቆዳ ስፋት ሲሰላ ወደ 26.2 ሚሊዮን ሄክታር አሳድጎታል። ከዚህም ባለፈ ቀድሞ በዓመት 92 ሺህ ሄክታር የነበረው የደን ውድመት በአሁኑ ወቅት ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

አረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የአየር ንብረት ፋይናንስ (Climate Finance)

መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ስኬቶች ባሻገር ሰፊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን እያስመዘገበ ይገኛል። በመላ ሀገራችን በተቋቋሙ 120 ሺህ በላይ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች አማካኝነት 767 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች፣ በተለይም ለሴቶች እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ከተተከሉ ችግኞች መካከል 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት እንደ ፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖ እና የከተማ ውበትን የሚጨምሩ ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት አግዟል።

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ያከናወነችው ተግባር አሁን ላይ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ገቢነት እየተቀየረ ይገኛል። ሀገራችን ደኖቿን በመጠበቅ እና አዳዲስ ደኖችን በማልማት ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሚዛን ለምታበረክተው አስተዋጽኦ የካርቦን ሽያጭ (Carbon Credit) ተጠቃሚ መሆን ጀምራለች። ይህ የአየር ንብረት ፋይናንስ (Climate Finance) ለሀገራዊ ጥቅል ምርት ዕድገት (GDP) አዲስ የገቢ ምንጭ ከመሆኑም ባለፈ፣ የኢትዮጵያአረንጓዴ ልማት ጉዞ በፋይናንስ ራሱን እንዲችል እያደረገው ነው።

የደኅንነት ዋስትና እና ቀጣናዊ ተጽዕኖ

የመርሐ ግብሩ ውጤታማነት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ረገድም ጉልህ ለውጥ አምጥቷል። በየዓመቱ ይከሰት የነበረው 1.9 ቢሊዮን ቶን የአፈር መሸርሸር በአሁኑ ወቅት ወደ 208 ሚሊዮን ቶን ዝቅ እንዲል መደረጉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ለሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ደኅንነት (ከደለል በመከላከል) ትልቅ ዋስትና ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ በመስጠት ረገድ እንደ ሞዴል እየተወሰደች ሲሆን፣ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በመስጠት ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረች ትገኛለች። ይህ አጠቃላይ ስኬት ኢትዮጵያ እአአ 2030 (2022 .) ካስቀመጠችው የ30 በመቶ የደን ሽፋን ግብ ለመድረስ ጉዞዋን ያፋጥነዋል።

በለሚ ታደሰ