የአንድ ሀገር የታሪክ ፍሰት ካቆለቆለበት አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ልዕልና የሚፈስሰው፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምሰሶዎቿም ጸንተው የሚቆሙት በመሪዋ የራዕይ አድማስ ስፋት፣ በፈተና ማዕበል ውስጥ በሚታይ የማይናወጥ ጽናት እና በተግባር በሚፈተን እልህ አስጨራሽ ትጋት ነው።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው በማታውቀው ውስብስብ ውጣ ውረድ፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ እንዲሁም የኅልውና ፈተና ውስጥ አልፋለች።
በዚህ አስፈሪ እና ፈታኝ ማዕበል መካከል፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በአስከፊ ጨለማ ውስጠ አንደ ተስፋ ብርሃን ወገግ በማለት፣ ሀገራችንን ከነበረችበት ጥልቅ የውድቀት እና የመበታተን ስጋት መንጥቆ በማውጣት ወደ አዲስ የተስፋ እና የብልፅግና ምህዋር አሸጋግሯታል።
ይህ የታሪክ መታጠፊያ፣ የማይቻለውን የመቻል፣ የተሰበረውን የመጠገን፣ የራቀውን የማቅረብ እና ተዳፍኖ የኖረውን የሀገር እምቅ አቅም ፈልፍሎ ለዓለም የማሳየት ረቂቅ ጥበብ የታየበት ነው።
ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር በማቆራኘት፣ የዜጎችን ሥነ-ልቦናዊ ስብራት በመደመር እና በይቅርታ ጠግኖ ለታላቅ ዓላማ የማሰለፍ ድንቅ ብቃት የተገለጠበት የታሪክ አሻራ ነው።
ዛሬ ላይ ይህ ተምሳሌታዊ መሪነት የዚህ ትውልድ መለያ መልክ፣ የኢትዮጵያም አዲሱ ገፅታ ሆኗል። ይህ ገፅታ በአረንጓዴ አሻራ በለመለሙ ተራራዎቻችን ኅያው ምስክርነት፣ በከተሞቻችን የኮሪደር ልማት እና ወንዝ ዳርቻዎች በተገለጠው ውበት እና ፅዳት፣ በስንዴ ማሳዎቻችን ሉዓላዊነት በተረጋገጠው የምግብ ነፃነት፣ እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂው ምጥቀት የሚገለጠው የታደሰች እና የበለፀገች ኢትዮጵያ ምስል ነው።
ባለፉት ዓመታት የታዩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላላቅ የአመራር ሥነ-ባህርያት እና ረቂቅ ጥበቦች የዚሁ አዲስ የኢትዮጵያ ትርክት ውጤቶች ሲሆኑ፤ ዋና ዋናዎቹን በሚከተለው ጥልቅ አገላለጽ ልናያቸው እንችላለን፡-
1. ከሀገር ፍቅር የሚመነጭ የራዕይ ልዕልና እና የ"መደመር" ሥነ-ልቦና
እውነተኛ መሪነት የሚጀምረው ሀገርን በጥልቀት ከመውደድ፣ ለክብሯ ከመቅናት እና የነገዋን ብሩህ ምስል ከሩቅ አሻግሮ ከማየት ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን፣ "መደመር" በተሰኘው ጥልቅ ሀገር በቀል ፍልስፍና ላይ የታነፀ ነው። ይህ ጥበብ ባለፉት ዘመናት የተገነቡ አወንታዊ የሀገር ወረቶችን በመጠበቅ፣ የታሪክ ስብራቶችን በእውቀት እና በይቅርታ በማረም፣ እንዲሁም ለወደፊቱ የሚያስፈልጉ የፈጠራ ውጤቶችን በማካተት ሀገርን ወደ ላቀ ከፍታ የማሸጋገር የረቀቀ ብቃት ነው።
መሪው የኢትዮጵያን የብዝኃነት ጸጋ እንደ መከፋፈያ ሳይሆን እንደ ውበት ጌጥ አድርገው በመሳል፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያሳዩት ፅናት የሀገር ፍቅራቸው ኅያው ማሳያ ነው።
2. የተወረወረን ድንጋይ ወደ ግንባታ የመቀየር እና ፈተናን የዕድል ማሳደጊያ የማድረግ ብቃት
የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። የውስጥ ፖለቲካዊ ሹክቻዎች፣ የውጭ ጫናዎች፣ ጦርነትና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውሶች ተደራርበውባት ነበር። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገጠሙትን ዙሪያ መለስ ማዕበሎች በማንገራገር ከማለፍ ይልቅ፣ ፈተናዎቹን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ሀገራችንን በጽናት አሻግረዋል።
"የተወረወረብንን ድንጋይ ለግንባታ እንጠቀምበታለን" በሚለው ብሂላቸው መሰረት፣ በጦርነትና በዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ ሆነው እንኳ የሀገር ውስጥ አቅምን በማጎልበት፣ የስንዴ ልማትን በማስፋፋት ሀገራችንን ከለማኝነት ወደ ውጭ ላኪነት አሸጋግረዋል። ይህ የማይቻል የሚባለውን የቆየ ትርክት የሰበረና ፈተናን ወደ ስኬት የቀየረ የልዕለ-አእምሮ መሪነት ጥበብ ነው።
3. የዲፕሎማሲ እና የጂኦ-ፖለቲካ አርቆ አሳቢነት
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላኛው ጥልቅ የአመራር ብቃት የሀገራችንን የጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ በሚዛን መጠበቅና ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ላይ ይገለጻል። የውኃ ላይ ፖለቲካን በአሸናፊነት በመምራት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከነበረበት የህልውና አደጋ ታድገው፣ የውጭ ኃይሎችን ጫና በመቋቋም በተሳካ ሁኔታ ውኃ እንዲይዝና ኃይል እንዲያመነጭ አድርገዋል። ከዚህም ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና ለማጠናከር፣ የባህር በር ለማግኘትና የባህር ላይ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጀመሩት ቆራጥ ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ፣ የሀገራችንን የረጅም ጊዜ ህልውናና የንግድ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጥ ታሪካዊ እርምጃ ነው። ሀገራችንን የብሪክስ አባል እንድትሆን በማድረግም የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን አረጋግጠዋል።
4. የተዳፈነ እምቅ አቅምን ገልጦ የማውጣትና ሀብት የማስተባበር ጥበብ
ኢትዮጵያ ያላትን ነባርና ያልተነካ የተፈጥሮ ጸጋ በማውጣት ተጨማሪ ገቢዎችንና የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የመሪው አስደናቂ ጥበብ ነው።
"የገበታ ለሸገር"፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች የመንግስትን መደበኛ በጀት ሳይነኩ፣ ህዝብን፣ ባለሃብቱን እና ተቋማትን በማስተባበር የተሰሩ የአመራር ብቃት ማሳያዎች ናቸው።
ማንም ዞር ብሎ የማያየውንና በቆሻሻ ተሞልቶ የነበረውን ስፍራ ወደ ዓለም አቀፍ የመዝናኛና ቱሪዝም ማዕከልነት የቀየሩት የእንጦጦ፣ የወንጪ፣ የኮይሻና የጎርጎራ ፕሮጀክቶች የዚህ የፈጠራ ስራ ኅያው ምስክሮች ናቸው። ይህ ጥበብ የሀገርን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ዜጎች በሀገራቸው ተስፋ እንዲያደርጉ ያስቻለ ነው።
5. ትጋት፣ ዕረፍት የለሽ የሥራ ባህልና የፕሮጀክቶች ሌት ተቀን ክትትል
በሀገራችን ለዘመናት የነበረውን የተጓተተ የፕሮጀክት አስተዳደር ባህል በመስበር በፍጥነት፣ በጥራት እና በከፍተኛ የውበት ደረጃ ስራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተግባር አረጋግጠዋል። ዛሬ ላይ ሀገራችን በቀናት፣ በሳምንታት እና በወራት የሚጠናቀቁ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚፈጠሩባት ሀገር ሆናለች። በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱት የኮሪደር ልማቶች የዚህ ፈጣን አፈፃፀም ማሳያዎች ናቸው። ይህ ስኬት የመነጨው ከመሪው የቅርብ ክትትል፣ ሌሊት ከቀን ከሚደረግ ያልተቋረጠ ምልከታ፣ እና ለላቀ የሥራ ባህል ካላቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ነው። ስራን በእጅ አዙር ከመምራት ይልቅ በቦታው ተገኝቶ አቅጣጫ ማስቀመጥን መለያቸው አድርገዋል።
6. የነገን ዓለም የመቅደም የዲጂታል ራዕይና የቴክኖሎጂ ሽግግር
መሪው ኢትዮጵያን ከትናንት የኋላቀርነት ታሪክ አላቅቀው ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር ለማራመድ ሰፋፊ ስራዎችን ሰርተዋል። የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂን በመንደፍ፣ የፋይዳ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያን በማስተዋወቅ ከ27 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ወደ ዘመናዊ ሥርዓት አስገብተዋል። የቴሌኮም ዘርፉን ሊበራላይዝ በማድረግና የቴሌ ብር ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ በአንድ ዓመት 16 ትሪሊዮን ብር እንዲያንቀሳቅስ አድርገዋል። ከዚህም በላይ የአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በመመስረት ትውልዱ በማህበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝም እና በዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያ ፈጠራዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
7. የአረንጓዴ አሻራ ራዕይ፡ ከጥርጣሬ ወደ አህጉራዊ ንቅናቄ
የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ሲጀመር ብዙዎች ራዕዩን ያልተረዱትና እንደ ፖለቲካ ቅንጦት የቆጠሩት ቢሆንም፣ በመሪው እልህ አስጨራሽ ትጋትና የህዝብ ማስተባበር ጥበብ ዛሬ ላይ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ይህ መላውን ህዝብ ያሰለፈ ታላቅ ንቅናቄ የሀገራችንን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ (በፍራፍሬ ልማት) አስተዋፅኦ አድርጓል፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝቷል። ለዚህም የዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) ታላቁን የ"አግሪኮላ ሜዳልያ" ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አበርክቶላቸዋል። ይህ ራዕይ መሪው ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ ደህንነት ያላቸውን አሳቢነት ያሳያል።
8. የሰው ተኮር ልማት እና አሳታፊ የፖለቲካ ባህል
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር በግዙፍ ፕሮጀክቶች ብቻ የተገደበ ሳይሆን "ሰው-ተኮር" በሆኑ የልማት ሥራዎችም የደመቀ ነው። ልማት ለሰዎች እንጂ ሰዎች ለልማት አይደሉም የሚለውን ዕሳቤ በመያዝ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች ዕድሳት፣ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ የአፍጥር፣ እና የመሶብ ማጋራት ንቅናቄዎችን በማስጀመር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን ደግፈዋል። ይህ የመሪነት ባህሪ ሩህሩህነትን፣ ማህበራዊ ፍትህን እና ከህዝብ ጋር መቆምን በግልፅ የሚያሳይ የሞራል ልዕልና ነው።
በአጠቃላይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት፣ ኢትዮጵያን ከነበረችበት የመበታተን ስጋት እና ስነ-ልቦናዊ ስብራት አውጥቶ፣ የተበታተኑ አቅሞቿን በማስተባበር ወደ ብልፅግና ምህዋር ያስገባ ነው።
ማዕበልን አብቅቶ፣ ፈተናን ወደ ጸጋ ቀይሮ፣ ቴክኖሎጂን ከጉልበት፣ ዕውቀትን ከትጋት ጋር አዋህዶ የማይቻለውን የሚቻል መሆኑን በተግባር ያሳየ የተምሳሌታዊ መሪነት ኅያው መማሪያ ነው።
በቀጣይም ሀገራችን ወደ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ስታመራ፣ እነዚህ የተዘሩ የለውጥ ፍሬዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የህዝቦቿን አንድነት እና አጠቃላይ ሀገራዊ ብልፅግናን ይበልጥ እንደሚያጸኑት አያጠራጥርም። ዐቢይነት—በዘመናችን የታየ፣ ቃልን ከተግባር፣ ራዕይን ከውጤት ጋር ያጋመደ የኢትዮጵያ የትንሣኤ መንገድ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ