በዓለም ታሪክ ውስጥ ፖለቲካዊ ሪፎርምን በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ እጅግ ፈታኝና ጥቂት ሀገራት ብቻ በድል የተሻገሩት የጠባብ ድልድይ ጉዞ ነው። እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያ ወይም የመን ያሉ ሀገራት የለውጥ ጥያቄዎችንና የፖለቲካ መነቃቃትን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻላቸው ወደ ፍርስራሽነትና የእርስ በእርስ ጦርነት አዘቅት ውስጥ ሲገቡ፤ በአንጻሩ እንደ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር ያሉ ሀገራት ደግሞ ሪፎርምን በጥበብና በአርቆ አሳቢነት በመምራት የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን በቅተዋል።
ወደ ሀገራችን ስንመጣ፣ ከ2010 ዓ.ም በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ በከፍተኛ የፖለቲካ ስብራትና የሕልውና አደጋ ውስጥ ተገኝታ ነበር። በሀሳብ ልዩነት ምክንያት ብቻ የሀገር ባለቤትነት ስሜትን የሚጋፉ አደገኛ ተጽዕኖዎች ተፈጥረው ነበር። ለዘመናት የተከማቹ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የማንነት፣ የወሰን፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሀገሪቱን ወደማትወጣበት ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ ከተዋት ነበር።
ከዚህ አስፈሪ ገደል አፋፍ ሀገሪቱን የታደገው ባለፉት ስምንት ዓመታት የተተገበረው ፖለቲካዊ ሪፎርም ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለውጥን የምታመጣው ክፉውንም ደጉንም በሚያፈርስና ወረትን በሚያወድም ቅጽበታዊ አብዮት ቢሆንም፣ የ2010ሩ ለውጥ ግን በሪፎርም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳካ ሰላማዊ ሽግግር የተደረገበት ነው። የዚህ ለውጥ ዋነኛ መዘውር የሆነው የ"መደመር" ዕሳቤ፣ የፖለቲካ ባሕላችንን ከጥላቻ፣ ከመፈራረጅና የሌላውን ሀሳብ ከማጥፋት አዙሪት በማውጣት ትናንትን ከዛሬ ጋር ያስታረቀ የጋራ አማካኝ መንገድ ፈጥሯል። የመደመር መንግሥት ባሕሪ፣ የትናንት በደሎች ላይ ጥፋተኛ በመፈለግ ጊዜ ከማባከን ይልቅ፣ የትናንት ጥፋቶችም ሆኑ ልማቶች የጋራ ታሪካችን መሆናቸውን አምኖ ብሩህ የጋራ ነገን መገንባት ነው።

ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ሊገነባ የሚችለው ገለልተኛና የሕዝብ አመኔታ ባላቸው ተቋማት መሆኑን የተረዳው የለውጡ መንግሥት፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እንዲሆኑ አድርጓል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የዕንባ ጠባቂ ተቋምና የጸጥታ አካላት በሕግና በኅሊናቸው ብቻ እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው የሀገርና የዜጎች ደኅንነት ዘብ እንዲሆኑ የአደረጃጀትና የሕግ ሪፎርም ተደርጎላቸዋል። ከዚህም ባሻገር፣ ጫፍና ጫፍ ቆመው የተቃርኖ ፖለቲካ ሲያራምዱ የነበሩ ኃይሎችን ለማቀራረብና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ታሪካዊ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ተደርጓል። ይህ እርምጃ ለዘመናት እርስ በእርስ ሲያጋድሉ የነበሩ አጀንዳዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሰፊ ዕድል የከፈተ ነው።
የለውጡ ሌላኛው አስደናቂ ስኬት የመግባባት ዴሞክራሲን በተግባር ማሳየቱ ነው ። "ያሸነፈ ሁሉንም ይወስዳል" ከሚለው ኋላቀር ፖለቲካ በመውጣት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በካቢኔና በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ተሳትፈው ሀገር እንዲመሩ ተደርጓል። ይህ አካታችነት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ከማስፋቱም በላይ ሀገራዊ አንድነትን በእጅጉ አጠናክሯል። እንዲሁም ለዘመናት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና በደሎችን በዘላቂነት ለመፍታትና ታሪካዊ እርቅ ለማውረድ የሚያስችል የተሟላ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ትግበራ በመግባት ላይ ይገኛል።
በአጠቃላይ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተደረገው የፖለቲካ ሪፎርም የኢትዮጵያን ስብራት የጠገነና የሀገረ-መንግሥቱን መሠረት ያጸና ነው። ምንም እንኳን በሂደቱ ውስብስብ የፀጥታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም፣ መንግሥት በሆደ-ሰፊነትና በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን ለመፍታት ያሳየው ቁርጠኝነት ሀገራችንን ወደ ብሩህ ተስፋ አሸጋግሯታል። በመደመር ዕሳቤ የታነጸው ፖለቲካዊ አውዳችን፣ የልዩነት ግድግዳዎችን በማፍረስ የኅብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ድልድይን በመገንባት የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ እጅግ ብሩህ አድርጎታል!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ