በታሪክ ማህደር ውስጥ አንዳንድ ወራት ከሌሎቹ ጎልተው የሚወጡት፣ የዘመናትን አዙሪት ሰብረው አዲስ ምዕራፍ ስለሚከፍቱ ነው። ለኢትዮጵያችን፣ መጋቢት እንዲህ ዓይነቱን ታሪካዊ ክብደት የተሸከመ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትና ኢትዮጵያውያን የሉዓላዊነት ጉዟቸውን በተጨባጭ ያረጋገጡበት ወር መጋቢት ነው ።
ከስምንት ዓመታት በፊት ወደነበረው የፖለቲካ ትዕይንት መለስ ብለን ስንቃኝ፣ የኢትዮጵያ ሰማይ የውጥረት ደመና አርግዞ የሀገራችን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መተንበይ የማይቻልበት ወቅት ነበር። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለው የወጣቶች የተቃውሞ ንቅናቄ፣ የለውጥ ጩኸትና የፍትህ ጥያቄ ሀገራችንን አናውጧት ነበር። ሥርዓቱ የሕዝቡን ጥያቄ የመመለስ አቅሙ ተሟጦ፣ ኢትዮጵያ በመጠፋፋት ፖለቲካና በትርምስ አዘቅት ውስጥ ገብታ በነበረችበት በዚያ ፈታኝ ወቅት ነው፣ ያ ሁሉ የሕዝብ ብሶትና የወጣቶች እልህ አስጨራሽ ትግል አምጦ አንድ ታሪካዊ ክስተት ወለደ።
ይህም ክስተት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ሥር የተበሰረው ታላቁ የለውጥ ምዕራፍ ነው ። ለመሆኑ፣ የሕዝብን መሻት አንግቦ የመጣው ይህ መጋቢት ምንን ቀየረ?
ይህ ጥያቄ ላለፉት ስምንት ዓመታት የተጓዝንበትን መንገድ መለስ ብለን እንድንቃኝና ያሳለፍናቸውን ስብራቶች፣ ያገኘናቸውን ድሎች፣ እንዲሁም የተሻገርናቸውን ፈተናዎች ሚዛን ላይ በማስቀመጥ የወደፊቱን አቅጣጫችንን እንድንተልም ይጋብዘናል።
ከልዩነት ፖለቲካ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት
ከመጋቢት 2010 ዓ.ም በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትዕይንት ወደኋላ ተመልሶ ለታዘበ ሰው፣ ኢትዮጵያ በዜጎች መካከል የ"አንደኛ" እና የ"ሁለተኛ" ደረጃ ዜግነት ስሜት የፈጠረ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎችን ብቻ የሀገርና የሥልጣን የበላይ ባለቤት ያደረገ ሥርዓት ሰፍኖባት እንደነበር ያስታውሳል። ፖለቲካው በጥላቻ፣ በመፈራረጅና በመጠፋፋት ላይ የተመሠረተ፣ የኃይል እና የጠመንጃ የበላይነት ጎልቶ የሚታይበት ነበር። በተለይም "የመሐልና የዳር" እንዲሁም "የዋና እና የአጋር" ክልሎች የሚል ከፋፋይ ግንብ ተገንብቶ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል የመወሰን መብት ተነፍገው ቆይተዋል። ይህ አካሄድ ኢትዮጵያን የብሔር ግጭቶች መፈልፈያና የጥርጣሬ ምድር አድርጓት ነበር።
የመጋቢቱ ለውጥ ግን ይህንን የተዛባና አድሏዊ የፖለቲካ ግንኙነት ከመሠረቱ በመናድ፣ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የሚያሸጋግር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል። ይህ ሽግግር በቃላት ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በተጨባጭ ተግባራትና በሕግ ማዕቀፎች ጭምር የተጠናከረ ነው። ለውጡ መጀመሪያ ያደረገው ነገር ቢኖር፣ ለዘመናት "አጋር" ተብለው የተገለሉትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደ መሐል የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት ማምጣት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ የእኩልነት ምድር እንድትሆን፣ ማንኛውም ዜጋ በማንነቱ ሳይገደብ በሀገሩ ሰማይ ሥር እኩል የመብትና የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓታዊ ለውጥ ተገኝቷል።
ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የጸናው ደግሞ የጋራ ታሪካችንን፣ የጋራ ሕመማችንንና የጋራ ተስፋችንን በማስተሳሰር ነው። ለውጡ ጥላቻን በምክንያት፣ መጠፋፋትን በውይይት፣ መገለልን ደግሞ በአካታችነት ተክቶታል። ከዚህ ቀደም እንደ ጠላት ይታዩ የነበሩና በስደት የቆዩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ መደረጉ፣ የወንድማማችነት የመጀመሪያው ተግባራዊ ማሳያ ነው። ይህም "ሀገራችን ለሁላችንም ትበቃለች" የሚለውን ታላቅ መንፈስ በዜጎች ልብ ውስጥ እንዲሰርጽ አድርጓል።
በአጠቃላይ፣ መጋቢት ኢትዮጵያን ከጠባብ የብሔር ፖለቲካ አዘቅት አውጥቶ ወደ ሰፊው የኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት አድማስ ማሸጋገሩ ነው። ይህ ወንድማማችነት በብዝኃነት ውስጥ ያለን አንድነት የሚያከብር፣ የአንዱ ጉዳት የሌላውም ሕመም መሆኑን የሚገነዘብና ነው።
ከነጠላ ትርክት ወደ አሰባሳቢ ራዕይ
አንድን ሀገር የሚያቆመው ጽኑ መሰረት የጋራ ትርክት ነው። ከመጋቢት 2010 በፊት የነበረው ትርክት፣ ያለፉ ዘመናትን በደሎች እየቆጠረና እየደጋገመ የሚቆዝም፣ ልዩነትን የሚያሰፋና ጥላቻን የሚሰብክ ነጠላ ትርክት ነበር። ይህ አጉል አዝማሚያ ሀገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ ጥሎት ቆይቷል።
የለውጡ መንግሥት ግን ይህንን አፍራሽ ትርክት ወደ አሰባሳቢና ገንቢ ራዕይ ለመቀየር "መደመር" የተሰኘውን ፍልስፍና አስተዋውቋል። መደመር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን በአዎንታዊነት የሚያስተሳስር፣ ኢትዮጵያውያን ከታሪክ እስረኝነት ወጥተው መልካሙን አውርሰው ወደፊት እንዲራመዱ የሚያስችል እሳቤ ነው። ብዝኃነትን እንደ እሴት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ደግሞ እንደ አቅም የወሰደ የወል ትርክት ግንባታ እየጎላ መጥቷል። ይህም በዜጎች መካከል ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን፣ ከጥርጣሬ ይልቅ መተማመንን የሚያጎለብት የህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት መሰረት ሆኗል።
ከጥገኝነት ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ብዝሃ ዘርፍ ልማት
የኢኮኖሚው ዘርፍ ከመጋቢቱ ለውጥ በፊት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነበር። ከፍተኛ የዕዳ ጫና፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መዛባት፣ እና በጥቂት ዘርፎች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እድገት የኢኮኖሚው መገለጫዎች ነበሩ። የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተገደበና ኢኮኖሚው በመንግሥት መራሽነት የተተበተበ ነበር።
ለውጡን ተከትሎ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (HGER 1.0 & 2.0) ተቀርፆ ወደ ተግባር በመገባቱ፣ ኢኮኖሚው ከመንግሥት መራሽነት ወደ ግሉ ዘርፍ መራሽነት እንዲሸጋገር ተደርጓል። በተለይም ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ደፋር እርምጃ ነው። የገንዘብ ምንዛሬ ሥርዓቱን ለገበያ ክፍት ማድረጉ፣ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት በማጥበብ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
የኢኮኖሚ ዕድገቱ በጥቂት ዘርፎች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ የተመሠረተ የብዝሀ ዘርፍ ዕድገት እንዲሆን አቅጣጫ ተይዟል። በዚህም ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ግብ ይዛ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ጥቂት ኢኮኖሚዎች ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል። የመንግሥት የታክስ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉና የወጪ ንግድ ገቢ መጨመሩ፣ ሀገራችን በራስ አቅም የመልማት አቅሟን እያሳደገች መሆኑን ያረጋግጣል።
የግብርና አብዮት፡ ከተረጂነት ወደ ላኪነት
ግብርና የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ቢሆንም፣ ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት ግን ኢትዮጵያ የረሃብና የልመና ተምሳሌት አድርጎ የሚያስቆጥር የታሪክ ጠባሳ ነበረባት። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ነበሩ።
የመጋቢቱ ለውጥ ግን ይህንን አሳዛኝ ታሪክ ቀይሮታል። "የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት" ጅማሮ ኢትዮጵያን ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት አሸጋግሯታል። በ2017/18 የምርት ዘመን ብቻ 29 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ማምረት መቻሉ የዚህ ትልቅ ስኬት ማሳያ ነው። "የሌማት ትሩፋት" ንቅናቄ ደግሞ በየቤቱ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የወተትና የማር ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና ለምርታማነት መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ቱሪዝምና ከተማ ልማት፡ የረሳነውን ጸጋ ወደ ኢኮኖሚ ሞተርነት
ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራትም፣ ለዘመናት ሳይለማና ለሀገር ገቢ ሳይሆን ቆይቷል። ከተሞቻችንም ቢሆኑ ለዘመናት በቂ ትኩረት ተነፍጓቸው፣ ለኑሮ የማይመቹና የሥነ-ውበት እሴት የጎደላቸው ሆነው ቆይተዋል።
በመጋቢቱ ለውጥ ግን፣ "የገበታ" ፕሮጀክቶች (ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ) ተቀርጸው፣ ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻዎች በከፍተኛ ፍጥነት ተገንብተዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ውበት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲውል አድርገዋል።
በተመሳሳይ፣ "ከተሞች በአዲስ ምናብ" በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ ከተሞችን የማዘመንና የማስዋብ ሥራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ነው። አዲስ አበባን ጨምሮ በ75 ከተሞች የተስፋፋው የኮሪደር ልማት፣ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ አረንጓዴና ለቱሪዝም ሳቢ አድርጓቸዋል።
ዲጂታል ሽግግር፡ ቴክኖሎጂ ለፈጣን ዕድገት
ከለውጡ በፊት የቴክኖሎጂና የዲጂታል አሰራር በሀገራችን እጅግ ኋላቀር ነበር። የቴሌኮም ዘርፉ በሞኖፖሊ የተያዘ፣ አገልግሎቱ ደካማና ውድ ነበር።
"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ፣ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት መሆኑ፣ እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መግባት ትልቅ እመርታ ፈጥሯል። የቴሌብር ስኬት የፋይናንስ አካታችነትን ያረጋገጠ ሲሆን፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል መቀየር ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ግልፅ አድርጎታል። ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" ንቅናቄ ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ለማብቃት የተጀመሩ የለውጡ ፍሬዎች ናቸው።
አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ፡ ሉዓላዊነትና የዓለም አቀፍ ተሰሚነት
በውጭ ግንኙነት ዘርፍ፣ ኢትዮጵያ ራሷን በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ቀደም ሲል የነበረው አጭር ርቀትና ስጋት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ፣ አሁን "ቅድሚያ ለጎረቤት" ወደሚልና ትስስርን ወደሚያጠናክር ፖሊሲ ተቀይሯል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ ኃይሎች ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከርና በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ያላትን ድምፅ ከፍ ለማድረግ የረዳ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። በተጨማሪም፣ ለዘመናት ታፍኖ የቆየው የባሕር በር ጥያቄ፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ትኩረት እያገኘ ይገኛል። ከዲያስፖራው ጋር የተፈጠረው ዜጋ-ተኮር ግንኙነትም ዳያስፖራውን እንደ ስጋት ከመመልከት፣ በሀገራዊ ልማትና ዲፕሎማሲ ቁልፍ አጋር ወደ ማድረግ አሸጋግሮታል። የሕዳሴው ግድብ በስኬት መጠናቀቅና የዓባይ ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ወደ ሥራ መግባቱ፣ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ልዕልና የሚያረጋግጡ ታላላቅ ክስተቶች ናቸው።
በመጨረሻም
እነዚህ ሁሉ ስኬቶች የተመዘገቡት አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ አይደለም። የሰሜኑ ጦርነት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫና እና የተፈጥሮ አደጋዎች የለውጡን ጉዞ ለመግታት ሞክረው ነበር። ሆኖም መንግሥት እና ሕዝብ እነዚህን ፈተናዎች በጽናት በመመከት፣ አንዳንዶቹንም ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ለውጡን ወደፊት ማራመድ ችለዋል።
መጋቢት 24፣ 2010 የኢትዮጵያ ዳግም ልደት የተበሰረበት ዕለት ነው። ባለፉት ስምንት ዓመታት የተጓዝንበት መንገድ የፖለቲካ ስብራታችንን የጠገንንበት፣ ኢኮኖሚያችንን በአዲስ መሠረት ላይ ያቆምንበት፣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብራችንን የመለስንበት ነው። መጋቢት የፈነጠቀው የብርሃን ጮራ፣ ዛሬ ላይ የሀገራችንን ገጽታ ቀይሮታል፤ የነገዋንም ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ አመላክቷል። የተገኘውን ድል ማስቀጠልና ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ ብልፅግና ማሸጋገር፣ የሁላችንም ታሪካዊ ኃላፊነት ነው። ጉዟችን ወደ ብርሃን ነው!
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ