ለጉብኝት ወደ ደቡብ አቸፈር የሚያቀኑ መንገደኞችን ቀልብ የሚስበውና በተፈጥሮ ውበት የታደለው “አባ ማታራት” (አሻር) ፏፏቴ፣ በግርማ ሞገስ ተቀምጦ እንግዶቹን ይጠራል።
ከባሕር ዳር - ዱርቤቴ መስመር 5 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ፣ ወደ ዳንግላ በሚወስደው አስፋልት አቅራቢያ በአብችክሊ ቀበሌ የሚገኘው ይህ ድንቅ ፏፏቴ፣ 21 ሜትር ቁመትና 35 ሜትር ስፋት ኖሮት በሦስት ቅርንጫፎች ተከፍሎ ቁልቁል ይወረወራል።
በበጋ ነጭ አረፋው ተፈትሎ እንደወረደ የጥጥ ገመድና እንደ ነጭ መቀነት ተጠቅልሎ የሚታይ ሲሆን፣ ድምቀቱም ለተመልካች ልዩ የዓይን እርካታን ይለግሳል።
የፏፏቴው ስያሜ ከአንድ አሳዛኝ አፈ-ታሪክ ጋር የተያያዘ መሆኑ ደግሞ ለጉዞው ተጨማሪ ትርጉም ይሰጠዋል።
በቀድሞ ዘመን አንዲት ሴት በክረምት ወራት ውኃውን ለመሻገር ስትሞክር በጎርፍ ትወሰዳለች፤ በፏፏቴው ኃይል የሚፈጠረው የእንፋሎት ጭስም ሴትዮዋን እንደሰወራት በማሰብ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ “ጭሱ የማታ እራት አደረጋት” በሚል “አባ ማታራት” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።
ፏፏቴው በግራር፣ በሾላ፣ በዶቅማና በሌሎች ጥቅጥቅ ያሉ አረንጓዴ ዕፅዋት የተከበበ በመሆኑ፣ አካባቢው በነፋሻማ አየርና በአበቦች መዓዛ ተሞልቶ እንግዶችን በደስታ ይቀበላል።
ይህ በደቡብ አቸፈር ወረዳ የሚገኝ የተፈጥሮ በረከት፣ ለቱሪስቶችና በተለይ ደግሞ ለተፈጥሮ አፍቃሪያን በጣም ምቹ መዳረሻ ነው።
በቢታኒያ ሲሳይ