Search

እኩል 3.98 ውጤት በማስመዝገብ በወርቅ ሜዳሊያ የተመረቁት ሁለት የጤና ዘርፍ ከዋክብት

ቅዳሜ መጋቢት 19, 2018 112

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዛሬ ካስመረቃቸው 255 የሕክምና ባለሙያዎች መካከል፣ ሁለት ስሞች በልዩ ክብር መድረክ ላይ በጉልህ ተደምጠዋል።
እነዚህ ወጣቶች በትጋትና በዓላማ መመሳሰል ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱም የ3.98 ድንቅ ውጤት በማስመዝገብ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን በወርቅ ሜዳሊያ አጠናቀዋል።
በፊዚዮቴራፒ የትምህርት ዘርፍ ኮከብ ሆና የወጣችው ፍቅር ገብሩ፣ ለስኬቷ ምስጢር ከግል ጥረቷ ባሻገር የቤተሰቦቿን ያልተቋረጠ ድጋፍ ትጠቅሳለች። "ለዚህ ውጤት ያበቃኝ የእኔ ትጋት ብቻ ሳይሆን፣ የቤተሰቦቼ ድጋፍና ክትትል ጭምር ነው" የምትለው ፍቅር፤ "ሰው ለዓላማው መሳካት ፈተናዎችን መቋቋም አለበት" የሚል ፅኑ እምነት አላት።
ፍቅር አሁን የያዘችውን እውቀት ተጠቅማ ነገ የተጎዱ ሰዎችን ለማከም እና ለማህበረሰቧ "የፈውስ እጅ" ለመሆን በጉጉት ትጠባበቃለች።
በሌላኛው የጤና ዘርፍ በነርሲንግ ደግሞ ነብዩ ዳዊት የልህቀት ማማውን ተቆጣጥሮታል። የነብዩ ስኬት የዛሬ ጅማሮ ሳይሆን ገና ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ የነበረ የትጋት ውጤት ነው።
ለነብዩ ነርሲንግ ማለት የጤና እውቀት ብቻ ሳይሆን፣ ሰብአዊነትና ስነ-ምግባር የታከለበት ታላቅ አገልግሎት ነው። "ማህበረሰቤን በቅንነት ማገልገል እፈልጋለሁ" የሚለው ነብዩ፣ ሀገራችን ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት በሙያው ለመደገፍ ቃል ገብቷል።
ፍቅር እና ነብዩ የውጤት ባለቤቶች ብቻ አይደሉም፤ ለብዙ ተማሪዎች አርአያ፣ ለወላጆቻቸው ኩራት፣ ለሀገራቸው ደግሞ አዲስ የጤና አርበኞች ናቸው።
በሳሙኤል ወርቃአየሁ