በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሐሳባቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ የቻሉበትን መድረክ በመፍጠር ረገድ ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ፡፡
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ የሚሰጡበት ዕለት ለመድረስ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተዋል፡፡
በዚህ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ፣ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦቻቸውን ለሕዝብ በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ አከናውነዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መድረክ በ19 ዙሮች የምርጫ ክርክር ያካሄዱ ሲሆን፤ ክርክሩም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ዲጂታል አማራጮች ለመራጩ ሕዝብ ተደራሽ ሆኗል፡፡
ሰብሳቢዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ እንደገለጹት መራጩ ሕዝብ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ድምፅ በመስጠት ወኪሎቹን እንዲመርጥ ለማስቻል የምርጫ ቅስቀሳና የክርክር ክህሎት ማዳበሪያ የተግባር ልምምድ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
በፖሊሲ ጥናት ምሁራን እና ባለሙያዎች በመታገዝም የፖለቲካ ፓርቲዎችን አማራጭ ሐሳብ ልዩነት እና ተመሳሳይነት የሚለካበት መረጃ በጥንቃቄ ተሰብስቧል፡፡
የክርክር ሂደቱን ቅርፅ እና ውጤታማነት ለማስጠበቅ ከሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር ተከታታይ ውይይት በመደረጉ፣ ፓርቲዎቹ ከተለምዷዊ አሠራር ወጣ ያለ ክርክር ማካሄድ ችለዋል፡፡
በክርክሩ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና የገለልተኛ ተቋማት ተወካዮች ጥያቄ የሚያቀርቡበት ዕድል በመፈጠሩ፣ ፓርቲዎቹ የሕዝብን ፍላጎት በቅርብ ተረድተው ራሳቸውን የለኩበት የክርክር ቅርፅ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡
ለዚህም ሲባል የክርክር መሪዎቹ ረጅም ጊዜ በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሠሩ እና ገለልተኝነታቸውን ለማረጋገጥ አስቀድሞ ለፓርቲዎች ተልኮ አስተያየት የተሰጠባቸው መሆኑን ሰብሳቢዋ ጠቅሰዋል፡፡
በምርጫ ሂደቱ የጥሞና ጊዜ ዜጎች በየቤታቸው ለማን ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው ሐሳብ የሚያሰላስሉበት መሆኑን ያነሱት ሰብሳቢዋ፣ ቦርዱ ሂደቱ ነጻ፣ ፍትሐዊ ተአማኒ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አበክሮ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የአፍሪካ ኅብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በታዛቢነት እንደሚገኙም ታውቋል፡፡
ሂደቱን ለመታዘብ ጥያቄ ላቀረቡ 16 የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትም ምላሽ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆኑ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡