“የቀረኝን ዕድሜ በሰላም ለመኖር እና ለልጆቼ መልካም ሀገር ለማውረስ እመርጣለሁ!” ይላሉ በ72 ዓመታቸው ለ7ኛ ጊዜ የሚመርጡት የአዳማው አባት።
በዕድሜ መግፋት እና በዘመናት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉት አዛውንቶች ስለ ሰላም እና ስለ ሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲናገሩ፣ ከአፋቸው የሚወጡ ቃላት ከተራ የፖለቲካ ትንተና ይልቅ የሕይወት ተሞክሮ ያጠራቸው እውነታዎች ሆነው እናገኛቸዋለን።
የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ72 ዓመቱ አንጋፋ አባት አቶ ፈይሳ መገርሳ በትክክል የዚህ እውነታ ማሳያ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በምትዘጋጅበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ አቶ ፈይሳ የዕድሜያቸውን መግፋት ሳይበግራቸው የምርጫ ካርዳቸውን በእጃቸው አስገብተዋል።
ይህ ምርጫ ለእርሳቸው ተራ ክስተት አይደለም፤ በሕይወት ዘመናቸው ለሰባተኛ ጊዜ ወደ ምርጫ ሳጥን የሚያመሩበት ልዩ አጋጣሚ እንጂ።
“ምርጫ የሚመረጠው ሕዝባዊ መንግሥት ለመምረጥ ነው። ወዶ ፈቅዶ በሚመርጡት መንግሥት ቅሬታ የለም፣ ክርክር የለውም። እኔ አሁን ዕድሜዬ 72 ዓመቴ ቢሆንም፣ የቀረኝን ዕድሜ በሰላም ለመኖር እና ልጆችም ጥሩ ሀገር ላይ እንዲኖሩ እምነት እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ። ጥሩ መንግሥት ከተመረጠ ዕድሜ ይጨምራል፤ በሰላም ትኖራለህ።” ሲሉ ይናገራሉ።
የዘንድሮ ምርጫ ከቀደሙት በምን ይለያል?
አቶ ፈይሳ ከዚህ ቀደም ስድስት ሀገራዊ ምርጫዎችን በቅርበት የታዘቡ በመሆናቸው፣ የዘንድሮውን ምርጫ ካለፉት ጊዜያት ጋር ለማወዳደር ሙሉ ብቃት አላቸው።
“ቀደም ሲል ደጋፊዎችን መደብደብና ማሰር፣ እንዲሁም መዋከብ ነበረ፤ የዘንድሮ ግን እስካሁን ምንም ዓይነት ኮሽታ ሳይኖር ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ እያቀረቡ ስለሆነ፣ ዴሞክራሲ የምንለውም እንደዚህ ነው። ፍራቻ ሳይኖር ወጥቶ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ፕሮግራሙን ማሳወቅ ነው፤ ሕዝቡም የሚበጀውን ይመርጣል።” ይላሉ።
ሕዝቡ የሚበጀውን፣ ነገ ለልጆቹ ሰላም እና ዕድገት የሚያመጣውን መርጦ እንደሚሰይም ሙሉ እምነት ያላቸው አቶ ፈይሳ መገርሳ፣ የዴሞክራሲ እውነተኛው መሠረት የዜጎች ነፃ ምርጫ መሆኑን በተግባር እያሳዩን ነው።
የዚህ አንጋፋ አባት ቁርጠኝነት እና ተስፋ፣ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ድርሻን በኃላፊነት የመወጣትን አስፈላጊነት የሚያስተምር ትልቅ ማሳያ ነው።