Search

"ምርጫ ካርዳችንን ይዘን የሚበጀኝን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል" - የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

ዓርብ ግንቦት 21, 2018 46

በመጪው ሰኞ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፃቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ ሦስት ቀናት ብቻ በቀሩበት በዚህ ወቅት ዜጎች መብታቸውን ተጠቅመው ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፡፡

በዚሁ ዙሪያ ሐሳባቸውን የሰጡት አቶ ቻላቸው አሰፋ "ምርጫ ካርዴን በጥንቃቄ ይዣለሁ፤ የሚበጀኝን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ" በማለት የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ንጉሤ በላይ በበኩላቸው የምርጫ ካርዳቸውን በጥንቃቄ በመያዝ ሰኞ ዕለት ድምፃቸውን ለመስጠት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ አክለውም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዜጎች የሀገራቸውን መንግሥት በራሳቸው ድምፅ የሚመርጡበት እና በዜጎች ፍላጎት ላይ መሠረት ያደረገ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሂደቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመላክታል፡፡