ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገራችን የሚካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ታዛቢ ልዑክ መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ-ካዚብዌ (ዶ/ር) ከምርጫ አስፈጻሚዎች እና ከሲቪል ማኅበራት ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር ውይይት አካሂደዋል።
በምክክር መድረኮቹ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት አመራሮች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ-ካዚብዌ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ጋር ያደረጉት ውይይት በምርጫ ዝግጅት፣ በአካታችነት፣ በዕለቱ በሚኖረው የጸጥታ ሁኔታ፣ በቅሬታ አፈታት እንዲሁም በውጤት አሰጣጥ እና ማስተላለፍ ሂደት ላይ ያተኮረ ነው።

በመድረኩ ቦርዱ የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባ ያከናወነበትን «ምርጫዬ» የተሰኘ የዲጂታል መተግበሪያን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም በውይይቱ ወቅት ተብራርተዋል።
የታዛቢ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር ያደረገው ምክክር ሴቶች በመልካም አስተዳደር እና በፖለቲካዊ ሂደቶች ውስጥ ባላቸው ሚና ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
በዚህም ፌዴሬሽኑ በሰላም ግንባታ እና በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ እያደረገ ያለውን ጥረት ገልጾ፣ በመላው ኢትዮጵያ ከ10 ሺህ በላይ የሰለጠኑ ሴት ታዛቢዎችን ማሰማራቱን ለታዛቢ ልዑኩ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ጋር በተደረገው ቆይታም ስለ ቅድመ ዝግጅት፣ የታዛቢዎች ስምሪት እንዲሁም ሰላማዊ፣ ተአማኒ፣ ግልጽና አካታች ሂደት እንዲኖር በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
ውይይቶቹ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒነት ያለው ሂደት እንዲኖር ለመደገፍ ኢጋድ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ያለው ሰፊ ግንኙነት አካል እንደሆነ ተገልጿል።
በላሉ ኢታላ