Search

የኢትዮጵያ የታሪክ መታጠፊያ፡- ከቁርሾ ወደ የጋራ ህልም

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 40

ሀገራችን ኢትዮጵያ አለመግባባቶችን ተመካክሮ የመፍታት የዳበረ እሴትና ቀደምት የሥልጣኔ መሠረት ያላት ቢሆንም አለመግባባት በተፈጠረ ቁጥር አጀንዳ አስርገው ለሚያስገቡ ታሪካዊ ጠላቶች ሀሳብን የምትፈታበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

በየዘመናቱ ከቅርብም ከሩቅም የተከፈቱባቸውን ጦርነቶች በመመከት ሀገር የማጽናት የወል ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዛሬ ደግሞ ታሪክ ራሱን ይደግም ዘንድ የሰላምና የልማት መሰናክል ለሆኑ ውስብስብ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በአንድነት ተሰባስበዋል።

የሰው ኃይል ሀብቷንና የተፈጥሮ ጸጋዋን አጣጥማ ወደፊት እንዳትራመድ ሰቅዘው ከያዟት ችግሮች ተላቅቃ የመደመር መንግሥት ይህንን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመጠንሰስ ቁልፍ የይቅርታና የምክክር መንገድ ጀምሯል።

በኢትዮጵያውያን የአኗኗር ሥርዓት ውስጥ ከግለኝነት ይልቅ ማህበራዊ ኑሮና አብሮነት ትልቅ ስፍራ ያለው በመሆኑ ዜጎች ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሮቻቸውን በራሳቸው ውይይት ለመፍታት መነሳታቸው የውስጥ አንድነትን የሚያጠናክርና የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ትልቅ ኃይል ሆኗል።

የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ መተማመንን ለመገንባት እና የትናንትን ቁስል በይቅርታ በማከም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተከናወነ ያለው ይህ ጉባኤ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የሲቪል ማህበረሰብ አካላትን፣ ሴቶችን እና ወጣቶችን በስፋት ያሳተፈና አካታች ነው።

በተለያዩ ክልሎች በተደረጉ መድረኮች ቀደም ሲል በአግባቡ የማይሰሙ የማኅበረሰብ ድምፆች ወደ ሀገራዊ ውይይት መምጣታቸውም የውይይትና የመከባበር ባህልን በማጎልበት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያስመዘገበ ይገኛል።

በሌላ በኩል ይህ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚመክሩበትና የአንድነት አቅማቸውን የሚያጎልብቱበት ታሪካዊ ጉዞ የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙ ለውስጥና የውጭ ኃይሎች በጋራ በመወያየትና የሀሳብ ልዩነታቸውን በመነጋገር መፍታት እንደሚችሉ በማሳየት ነው።

እንዲሁም ጦርነት የዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፉና መሠረተ ልማቶችን ከማውደሙ ባሻገር የሀገርን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስር የሚጎዳ በመሆኑ ውይይትን እንደ ብቸኛ አማራጭ መውሰድ የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም በዲፕሎማሲ መድረክ ተሰሚነትን ለመጨመር ወሳኝ ነው።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ስኬታማ የሚሆነው ሂደቱ አካታች ገለልተኛ ግልጽ እና ተግባራዊ ሲሆን እንደሆነ ታምኖበት እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን የሁሉም ወገኖች ቅን ተሳትፎና መደማመጥ ታክሎበት ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪትና ከድህነት ወጥታ ወደ ከፍታዋና የቀደምት ሥልጣኔ ዳግም ትንሣኤዋ በጽናት እንድትጓዝ የሚያስችላት መሠረት እንደሚጥል ይታመናል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: