Search

በአንድነት የለበስነው አረንጓዴ ካባ፡- ከችግኝ ተከላ እስከ ትውልድ ግንባታ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 99

ሀገራችን እያካሄደችው የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የተራቆተ መሬትን መልሶ ለማልማትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመረ ታሪካዊና ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

ይህ ንቅናቄ የዛሬውን ማኅበረሰብ ፍላጎት እያሟላ ለነገው ትውልድ የተረጋገጠ ህልውና እና የበለፀገች ለምለም ሀገር የማስረከብ ዘመን ተሻጋሪ ራዕይን ያነገበ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም እጅግ አስደናቂ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል።

የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ዋና ነዳጅ ህዝባችን በእድሜ፣ በጾታ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት እና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያይ ከህፃናት እስከ አዛውንት፣ ከመንግሥት ሰራተኞች እስከ ግል ባለሀብቶች ድረስ በአንድነት በመሰለፍ ያሳየው ሰፊ ተሳትፎና ሀገራዊ ህብረት ነው።

ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን በአንድ ቀን በማስተባበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል እንደሚቻል በተግባር በማሳየት፣ ሌሎች ሀገራት ህዝባቸውን ለአካባቢ ጥበቃ እንዴት ማነሳሳት እንዳለባቸው ትልቅ ማሳያ ሆናለች።

በትክክለኛ አመራርና በህዝብ ተነሳሽነት መንግሥትና ህዝብ ባደረጉት ተከታታይ እንክብካቤም ችግኞቹ በከፍተኛ ሁኔታ በመፅደቃቸው የተራቆቱ ተራራዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ ምንጮች እንደገና መፍለቅ ጀምረዋል፤ የከርሰ ምድር ውኃ በልፅጓል፤ እንዲሁም የሀገራችን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መርሐ ግብሩ ዛፍ የመትከል ሥራ ብቻ ሳይሆን ከአየር ንብረት ጥበቃ ባለፈ በቀጥታ ከኢኮኖሚ ብልፅግና ጋር የተሳሰረ ነው።

ከተተከሉት ችግኞች መካከል እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ እንጆሪ እና ቡና ያሉ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው የፍራፍሬና የኢኮኖሚ ተክሎች በመካተታቸው፣ ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አዲስ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ አዲስ ዕይታን ፈጥሯል።

በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር የማይበግረው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በማጋራት የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የቀጣናዊ ትብብርና የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ተሞክሮን በተግባር አስተዋውቃለች።

ይህ ስኬት ትላልቅ የገንዘብ በጀቶችን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ በውስጥ አቅምና በህዝብ አንድነት ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ለዓለም ያሳየ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እንደ ትልቅ አርዓያና ተጠቃሽ ተሞክሮ እየቀረበ ይገኛል።

በመሆኑም ይህ ለልጆቻችን የተራቆተች ሳይሆን አረንጓዴና ምርታማ ሀገር የማውረስ ትልቅ የትውልድ ፕሮጀክት በመሆኑ፣ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ በመቀጠልና እንክብካቤውን ባህል በማድረግ ታሪካዊ ዐሻራችንን ለትውልድ ማኖር ይኖርብናል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: