የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባውን የላቀ ማዕከላዊ ላቦራቶሪ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በተገኙበት አስመርቋል።
ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የረቀቁ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች መትከልን ብቻ የሚያበስር ሳይሆን እውቀትን ወደ ሙያዊ ብቃት፣ ምርምርን ወደ ፈጠራ፣ ፈጠራን ደግሞ ለሀገራዊ አገልግሎት ወደሚውሉ ተግባራዊ መፍትሔዎች የሚቀይር አዲስ የተቋማዊ አቅም ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
ላብራቶሪ የሠራዊቱን ሁለንተናዊ የዘመናዊነት ጉዞ የሚያፋጥን፣ የተቋሙን የቴክኖሎጂና የምርምር መሠረት የሚያጎለብት እንዲሁም የወደፊት ሀገራዊ ደኅንነትን በፅኑ መሠረት ላይ የሚጥል ታላቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥታት መካከል ያለውን ዘመናትን የተሻገረ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ የሁለትዮሽ ትብብሩ ወደ ሀገራዊ ደኅንነት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምዕራፍ መድረሱን ያሳየ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ በሳይበር ደኅንነት እና በላቁ የመከላከያ ሳይንሶች ዙሪያ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን፣ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን የምታፈልቅበትና የባለቤትነት አቅም የምትገነባበት ሰፊ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።
ላቦራቶሪው የተለያዩ የላቁ የኢንጂነሪንግ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና ሳይንሳዊ የምርምር ዘርፎችን በአንድ ማዕከል ያካተተ የቴክኖሎጂ ሽግግር መሆኑ ተገልጿል።
የላቀ የላቦራቶሪ ማዕከሉ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ትብብር የተገነባ ሲሆን፣ በውስጡ 7 ግዙፍ ላቦራቶሪዎችን የያዘ መሆኑ ተመላክቷል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ጀነራል መኮንኖች፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ልዑካንና ወታደራዊ አታሼዎች የተገኙ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው ችግኝ በመትከልም የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
በብርቱካን አስናቀ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: