የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን ማረጋገጥ ለሀገር ብሔራዊ ደኅንነት ጉልህ ሚና እንዳለው በማመን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ችግኝ በመትከል የዘንድሮውን ዓመታዊ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ መርሐ-ግብር በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመድረኩ ላይ እንዳብራሩት፣ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተካሄዱት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
በተለይም የሀገራችንን የተራቆተ መሬት በተለያዩ ተክሎች በማልበስ የደን ሽፋንን ማሳደግ መቻሉን ያነሱት አምባሳደሩ፤ አሁን ላይ እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን አረንጓዴ ውጤት በአካል መመልከት እና ማጣጣም መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አሰፋ አብዩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ላይ የሚፈጸሙ ውድመቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማኅበረሰብን ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥሉ አስገንዝበዋል፡፡
በሥነ-ምኅዳር መራቆት ምክንያት የሚከሰት የዝናብ እጥረት፣ የመሬት መሸርሸርና ድርቅ ምርታማነትን በመቀነስ ሕዝቦችን ለምግብ እጥረትና ለፍልሰት በመዳረግ ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ ስለሚከት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች እየተከናወኑ ያሉ የተፈጥሮ እንክብካቤ እና የልማት ሥራዎች እንደ አንድ ብሔራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ስምሪት ተደርገው እንደሚወሰዱ ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ በዘንድሮው መርሐ-ግብር ሁሉንም ሠራተኞች ባሳተፈ መልኩ ችግኝ ለመትከል ሰፊ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን፣ ተቋሙ ለኢቢሲ በላከው መረጃ መሠረት ባለፉት ሰባት ዓመታት በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄዎች ከ307 ሺህ በላይ የዛፍ፣ የፍራፍሬ እና የውበት ዛፍ ችግኞችን በማዘጋጀት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲተክሉ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ ሲወጣ ቆይቷል፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: