Search

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት 25.4 ቢሊዮን ብር አጸደቀ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 45

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 3ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን በስኬት በማጠናቀቅ፣ የክልሉን የ2019 ዓመታዊ በጀት 25.4 ቢሊዮን ብር አድርጎ አጽድቋል።

ይህ ለቀጣዩ ዓመት የጸደቀው በጀት ከ2018 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ30 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ለክልሉ የልማት ጉዞ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነው።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ ለምክር ቤቱ እንዳብራሩት፣ ከጸደቀው ጠቅላላ በጀት ውስጥ 61 በመቶ ያህሉ ከክልሉ የውስጥ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ከፌደራል መንግሥት ድጎማና ከተለያዩ ምንጮች የሚገኝ ይሆናል።

ይህ የውስጥ ገቢን የማሳደግ አቅም ክልሉ በራሱ አቅም ልማቶችን ለማፋጠን እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያመላክት ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የከተማ ልማትና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም የተመደበው ይህ ዓመታዊ በጀት የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይሁን እንጂ በጀቱ በፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ መሠረት ብቻ በጥንቃቄ ሥራ ላይ እንዲውል በአጽንኦት አሳስበዋል።

በተያያዘም ምክር ቤቱ የተሻሻለ የገቢ ግብር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅን፣ የክልሉን የፋይናንስ አስተዳደር ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅን፣ እንዲሁም የ2018 ተጨማሪ በጀት መወሰኛ ረቂቅ አዋጅን በዝርዝር መርምሮ በማጽደቅ ጉባኤውን በስኬት አጠናቋል።

በጀማል አህመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: