ኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታካሂደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ቀጣይነት ባለው የአካባቢ ጥበቃ እና ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ አልፎ፣ ለሀገራዊ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።
የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣቸውን ተጽዕኖዎች በመቋቋም እና የግብርናውን ዘርፍ በማጠናከር ረገድ መርሐ ግብሩ ያመጣቸው አዎንታዊ ውጤቶች በግልጽ እየታዩ ነው።
ከዚህ ቀደም የነበረው የደን መጨፍጨፍ፣ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መበላሸት የግብርና ምርታማነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ ጥሎት የቆየ ተደራራቢ ፈተና ነበር። ሆኖም ባለፉት ዓመታት የተካሄደው ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ይህንን በመቀየር ረገድ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሁን ላይ ከጥቅጥቅ ደን ችግኞች ባሻገር ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ ተክሎች ላይ ትኩረት አድርጓል። በዚህም እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና ያሉ ዘላቂ ጥቅም ያላቸው ችግኞች በስፋት በመተከላቸው የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው።
በመርሐ ግብሩ የተጠበቁ አካባቢዎችና የተተከሉ የመኖ ተክሎች ለወተትና ሥጋ ምርታማነት አስፈላጊውን የእንስሳት መኖ በማቅረብም የእንስሳት ሀብትን በማሳደግ ረገድ የበኩሉን ሚና እየጫወተ ይገኛል። የአበባና የዕፅዋት ሽፋን መጨመር ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ተጨማሪ የገቢ እና የምግብ ምንጭ መሆን ችሏል።
የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትለውን ድርቅ፣ የዝናብ እጥረት እና ጎርፍ ለመከላከል ተፈጥሮን ማደስ ወሳኝ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም ይህንን የአካባቢውን አየር ንብረት በማሻሻል አርሶ አደሮች ያልተጠበቁ የአየር ንብረት አደጋዎችን የመቋቋም አቅማቸውን እንዲገነቡ አስችሏቸዋል።
መርሐ ግብሩ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የአካባቢ ጥበቃ የተቀናጀ ስትራቴጂ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የግብርና መሰረት የሚያጠናክር፣ የአፈር እና ውኃ ሀብትን የሚንከባከብ ስልታዊ የልማት እንቅስቃሴም ጭምር ነው።
የመሬት ምርታማነትን በማሳደግ፣ የውሃ ሀብትን በመጠበቅ እና ለዜጎች ተጨማሪ የገቢና የምግብ ምንጮችን በመፍጠር ረገድም የምግብ ዋስትናን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ መሠረታዊ መፍትሔ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: