Search

የሳይንስ ሀቅ እና የፖለቲካ ሴራ፡- የግብፅ ግዙፍ የውኃ ብክነት እና የኢትዮጵያ ፍትሐዊ የመልማት መብት

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 32

ግብፅ በዓለም አቀፍ መድረኮች በየጊዜው የምታቀርበው የውኃ እጥረት ስጋት እና በኢትዮጵያ ላይ የምታካሂደው የፖለቲካ ውዥንብር ከተጨባጭ ሳይንሳዊ እና ሃይድሮሎጂካዊ ሀቆች ጋር እጅግ የተራራቀ ነው።

ሀገሪቱ ከምትጠቀመው የንጹሕ ውኃ መጠን ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው መነሻውን ኢትዮጵያ ካደረገው የዓባይ ተፋሰስ የሚገኝ ነው፡፡

ግብፅ በየዓመቱ በገዛ ግዛቷ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኪዩብክ ሜትር ንጹሕ ውኃ በትነት እንዲባክን ታደርጋለች።

በሃይድሮሎጂ ሳይንስ የተረጋገጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የግብፅ ዋና ችግር የላይኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ልማት ሳይሆን፣ በራሷ መሠረተ ልማቶች እና በባህላዊ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓቷ ምክንያት የሚከሰተው ከፍተኛ የውኃ ብክነት ነው።

በአስዋን ከፍተኛ ግድብ በተፈጠረው የናስር ሐይቅ አካባቢ ያለው የውኃ ትነት መጠን በሳይንሳዊ መንገድ ስንመለከት ሐይቁ የሚገኝበት የላይኛው ግብፅ ግዛት እጅግ ሞቃታማ እና በረሃማ ቀጣና በመሆኑ አብዛኛው ውኃ የበረሃ ሲሳይ ይሆናል።

በሳተላይት መረጃዎች፣ በSEBAL እና በPenman ሳይንሳዊ ሞዴሎች የተረጋገጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ከናስር ሐይቅ በየዓመቱ በትነት ምክንያት ብቻ ከ10 እስከ 16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ወደ አየር ይተናል።

ሌሎች የሃይድሮ-ሜቲዮሮሎጂ ሞዴሎች ደግሞ ይህ የትነት መጠን እስከ 18 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ያደርሱታል። ይህም ማለት ግብፅ ከዓባይ ወንዝ በየዓመቱ ከምታገኘው አጠቃላይ የውኃ ድርሻ እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን በትነት መልክ ታባክናለች ማለት ነው። በተጨማሪም በሐይቁ ዳርቻ የሚገኙ ጥልቀት የሌላቸው ሰፋፊ የውኃ አካላት ለዚህ ብክነት ትልቁን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ከአስዋን ግድብ ባሻገር በ1990ዎቹ መጨረሻ የተጀመረው የቶሽካ የበረሃ ፕሮጀክት ሌላው ግዙፍ የውኃ ብክነት ማሳያ ነው።

በሙባረክ ፓምፕ ጣቢያ በኩል በየዓመቱ 5.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ንጹሕ የዓባይ ውኃ ወደ ምዕራባዊው በረሃ የሚሳብ ሲሆን፣ የአካባቢው የትነት ምጣኔ በቀን እስከ 15 ሚሊሜትር በመድረሱ ምክንያት ከፍተኛ የውኃ መጠን በከንቱ ይባክናል።

በዚሁ በረሃ ላይ የተፈጠሩት የቶሽካ ሐይቆች እ.አ.አ ከ2002 እስከ 2006 ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ 12.69 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር ውኃ በትነት ያጡ መሆናቸው ይጠቀሳል። ይህም በዓመት በአማካይ 3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ያለምንም የግብርና ጥቅም በከንቱ መባከኑን ያረጋግጣል።

በግብርናው ዘርፍ የሚታየው የውኃ አጠቃቀምም በተመሳሳይ የቴክኖሎጂ እና የአስተዳደር ክፍተት የሚታይበት ነው። ግብፅ ከምትስበው አጠቃላይ 78 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ውስጥ 86 በመቶ የሚሆነውን (ወደ 67 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር) ለግብርና ዘርፍ የምታውል ቢሆንም፣ በናይል ሸለቆ እና ዴልታ ነባር መሬቶች ላይ የሚካሄደው የወለል ወይም የጎርፍ መስኖ አጠቃቀም ቅልጥፍና ከ50 እስከ 60 በመቶ ብቻ ነው።

ይህም ማለት ለመስኖ ከሚውለው የውኃ መጠን ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው በመስረግ እና ባልተደራጁ የማሰራጫ ቦዮች ምክንያት ይባክናል ማለት ነው። ሀገሪቱ በየዓመቱ የምታባክነውን አጠቃላይ የውኃ መጠን ስንደምረው ከአስዋን ሐይቅ የሚተነው 16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ፣ ከቶሽካ ሐይቆች እና ቦዮች የሚተነው 3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንዲሁም በመስክ ደረጃ የሚባክነው ከ25 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ በአጠቃላይ በየዓመቱ ከ35 እስከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ንጹሕ ውኃ ታባክናለች።

ግብፅ ይህን ያህል ግዙፍ የውኃ መጠን ባታባክን እና የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችን ብታደርግ ኖሮ ታላቅ የኢኮኖሚ እና የውኃ ደኅንነት ተጠቃሚ በሆነች ነበር።

ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በናስር ሐይቅ ዳርቻ የሚገኙ ጥልቀት የሌላቸውን ኾሮች ከመስመር በመቁረጥ እና የሐይቁን ወለል በማስተካከል ብቻ በዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ከትነት ማዳን ይቻላል።

በተጨማሪም የጎርፍ መስኖን ወደ ዘመናዊ የጠብታ እና የርጭት መስኖ በማሸጋገር ከ15 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር በላይ ውኃ ማዳን እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ይህም ግብፅ በየዓመቱ የምግብ እህል ገቢ ለማድረግ የምታወጣውን እና በ"ቨርቹዋል ውኃ" መልክ የምታስገባውን 30 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የውኃ እጥረት ሙሉ በሙሉ ለማካካስ የሚያስችል ነው።

ነገር ግን ግብፅ እነዚህን በገዛ እጇ የምታባክናቸውን የውኃ ሀብቶች በሳይንሳዊ መንገድ ከማስተካከል ይልቅ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውኃ መጠን በምታበረክተው ኢትዮጵያ ላይ የሤራ ፖለቲካ እና የሐሰት ወቀሳ መሰንዘርን መርጣለች።

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌት ሙሉ በሙሉ አጠናቅቃ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በጀመረበት በአሁኑ ወቅትም ቢሆን፣ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም በግብፅ የውኃ ድርሻ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱ የኢትዮጵያን ቅን እና ፍትሐዊ አቋም በተግባር አስመስክሯል።

የሕዳሴው ግድብ ሙሌት ከተጠናቀቀ በኋላም ግብፅ ያለምንም የውኃ እጥረት ችግር የቀደመውን አስተዳደራዊ እና ባህላዊ የውኃ አጠቃቀም መንገዷን በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥላለች።ይህም የኢትዮጵያ ልማት ስጋት አለመሆኑን እና የግብፅ ባለሥልጣናት የሚያነሱት አጀንዳ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተሸረበ መሆኑን ቁልፍ ማሳያ ነው።

ግብፅ በበረሃ ላይ ውኃ ማከማቸቷን እና በባህላዊ የመስኖ ዘዴዎቿ በየዓመቱ በአስር ቢሊዮን የሚቆጠሩ ኪዩብክ ሜትር ውኃ ማባከኗን ቀጥላ፣ በኢትዮጵያ ፍትሐዊ የልማት ሥራዎች ላይ የምታካሂደው ተቃውሞ እና የፖለቲካ ጫና ከእንግዲህ የሚያስኬድ አይደለም።

ለግብፅ ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ለቀጣይ የውኃ ደኅንነቷ የሚያዋጣት መንገድ በሀገሯ ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የውኃ ብክነት መቆጠብ እና የውኃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂዎቿን ማዘመን የመጀመሪያው መፍትሔ ነው፡፡

ውኃን በቅዝቃዜው የኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች ላይ ማከማቸት ያለው ሃይድሮሎጂካዊ ጥቅም ተረድታ ከኢትዮጵያ ጋር በተቀራረበ መልኩ በፍትሐዊነት እና በትብብር መሥራትም ሌላኛው ትልቅ መፍትሔ ነው።

ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን ከጀመረችው ሉዓላዊ ልማቷ የማያስቆማት በመሆኑ የግብፅ ድካም ሁሉ ከንቱ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ 

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: