Search

"ሀገር የሞተ እንደሆነ ወዴት ይደረሳል?"፡- ሀገርን ለማዳን ያገኘነው ወርቃማ ዕድል

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 33

"እናት አባት ቢሞት፣ በሀገር ይለቀሳል፤

ወንድም እህት ቢሞት፣ በሀገር ይለቀሳል፤

ሀገር የሞተ እንደሆነ፣ ወዴት ይደረሳል?"

እነኝህ ስንኞች ለወግ ማጣፈጫ የተፈጠሩ ሥነ ቃሎች አይደሉም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በደሙ ውስጥ የሚተነፍሰው፣ ሀገር ማለት በወሰን ከተከለለ መሬት ባለፈ የሥነ-ልቦና እረፍት እና የኅልውና የመጨረሻ መጠጊያ መሆኗን የሚያስረግጡልን የዘመናት ወርቃማ ፍልስፍናችን ናቸው።

ሰው የቱንም ያህል ቢሰበር፣ የሚወደውን ቢያጣ፣ ወድቆ የሚነሳበት እና ሀዘኑን አውጥቶ የሚጠገንበት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መደገፊያው ሀገር ናት።

ነገር ግን ያቺ መጠጊያ ሀገር ራሷ ስትፈርስ፣ የሰው ልጅ የመጨረሻ አድራሻው ተስፋ ቢስነት ይሆናል።

አባቶቻችን "የሀገሬ አፈር ይብላኝ" ሲሉ መሬቱን እንደ ተራ አቧራ ቆጥረውት ሳይሆን፣ የነፃነት እና የክብር መገለጫ የሆነችውን ሀገር ከመደራደሪያ በላይ መሆኗን ስለሚያውቁ ነው።

ለዚህም ነው ከዓድዋ እስከ ካራማራ ግላዊ እና ቡድናዊ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው የጋራ ኅልውናቸውን ያለ ልዩነት በደማቸው ጠብቀው ያቆዩልን።

የተሰበረው የመነጋገር ባህል እና የከፈልነው መሪር ዋጋ

ታዲያ ያንን የመሰለ ወርቃማ ታሪክ እና የሀገር ፍቅር ይዘን ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት ምን እንታዘባለን?

የውጭ ጠላትን በአንድነት የመመከት ታሪካዊ ጥንካሬያችንን በውስጥ ፖለቲካችን የሐሳብ ልዕልናን በማክበር እና የንግግር ባህልን በማዳበር ረገድ መድገም አልቻልንም።

ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ ሐሳብን በጉልበት ለማፈን መሞከር፣ የፖለቲካ ሥልጣንን በጠብመንጃ አፈሙዝ ለማረጋገጥ መነሳት የዘመናችን ትልቁ የሞራል ክስረት ሆኗል።

በሀገራችን የነበሯትን ቱባ የሽምግልና እና የሰላም እሴቶች ወደ ዘመናዊው ፖለቲካ ማሸጋገር ተስኖን አሸናፊ እና ተሸናፊን ብቻ የሚፈጥር የዜሮ-ድምር ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ቆይተናል።

ይህ የመደማመጥ ባህል ማጣት ያስከፈለን ዋጋ ቀላል አይደለም። "አረንጓዴ አፈር ላይ ተቀምጦ መራብ" የሚል ልብ ሰባሪ ታሪካዊ ተቃርኖ ውስጥ ወድቀናል።

ሰፊ ለም መሬት፣ በቂ ውኃ እና አምራች ኃይል ይዘን፣ ግጭት በፈጠረው አለመረጋጋት የተፈጥሮ ጸጋችንን ወደ ሀብት መቀየር ተስኖን የምግብ ዋስትናችንን አጥተናል።

ከዚህም በባሰ ለጎረቤት ሀገራት ስደተኞች የሰላም መጠጊያ የነበረችው ሀገራችን፣ የገዛ ዜጎቿ በገዛ ቀያቸው በብሔር ማንነታቸው ብቻ የሚፈናቀሉባት፣ ክብር አጥተው በበረሃ እና በባሕር የሚንከራተቱባት ምድር ሆናለች።

ይህ የቀደምት አባቶችን መስዋዕትነት የሚያራክስ እጅግ የሚያሳዝን የታሪካችን ቁልቁለት ነው።

ከፊታችን የቀረበው ወርቃማ ዕድል

ዛሬ ይህንን የመጠፋፋት አዙሪት ሰብረን የምንወጣበት ታሪካዊ እና ወርቃማ ዕድል ከፊታችን ተዘርግቷል።

ይኸውም የሀገራዊ የምክክር ሂደት ነው። ይህ ሂደት ላለፉት ዘመናት ያልሞከርነውን፣ ነገር ግን ሀገርን በጥንካሬ ለማቆየት ብቸኛው መንገድ የሆነውን "በሐሳብ የመሸናነፍ እና የመደማመጥ" ባህል በተግባር የምናሳይበት ትልቅ ድልድይ ነው።

ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ፣ ያቆሰሉንን እና ያቃቃሩንን መዋቅራዊና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች አውጥተን የምንወያይበት፣ የኃይል እርምጃን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የምንተካበት ሰፊ ምህዳር ተፈጥሮልናል።

ዕድሉን ካመከንነው የሚጠብቀን ኪሣራ

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዛሬ ቆም ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። ይህንን የተዘረጋልንን ወርቃማ ዕድል ብናመክነው፣ ሂደቱን በይስሙላ ለማለፍ ብንሞክር፣ ወይም በምክክሩ የሚደረስባቸውን መግባባቶች እና የፖሊሲ ሐሳቦች ወደ መሬት ሳናወርድ ቀርተን ጥርጣሬን ብናነግስ ምን እንሆናለን? መልሱ አጭር እና አስፈሪ ነው።

መጨረሻችን በሰላማዊ መንገድ ላይ ያለውን ተስፋ አሟጦ፣ ሀገርን ሙሉ በሙሉ ወደማያባራ ምስቅልቅል እና መበታተን መክተት ነው።

ያኔ መነሻችን ላይ ወዳነሳነው ጥያቄ እንመለሳለን... "ሀገር የሞተ እንደሆነ ወዴት ይደረሳል?"

እናት አባቶቻችን በደማቸው አጽንተው ያቆዩልንን ሀገር፣ እኛ በሐሳብ ልዕልና፣ በመቻቻል እና በእውነተኛ ምክክር አድሰን እና አልመን ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ታሪካዊ አደራ አለብን። ይህ ደግሞ ዕድለኛ ትውልድ ያደርገናል። ዕድለኝነታችን ግን እውነት የሚሆነው የተሰጠንን በአግባቡ ከተጠቀምን ብቻ ነው።

ጊዜው የጠብመንጃ አፈሙዝን ዝም አሰኝተን፣ የሰላምን እና የምክክርን ድምጽ ከፍ የምናደርግበት ነው።

ምርጫው የኛው ነው! ወይ በምክክር ታላቅ ሀገር መገንባት ወይም በግትርነት የመጨረሻዋን መጠጊያችንን ማጣት።

ቆም ብለን እናስብ፤ እያንዳንዳችን ለዚህች ታላቅ ሀገር ኅልውና እና ሰላም ምን እያደረግን ነው? ስብራታችንን እየጠገንን ነው ወይስ ክፍተታችንን እያሰፋን? መለስ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ!

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: