Search

በሐሳብ ልዕልና ሀገራዊ መግባባትን እንገነባለን

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 39

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጉዞ ውስጥ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው እና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠረው በኃይል አማራጭ ሳይሆን በሥልጡን የሐሳብ ማዕድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በአንድ ወቅት እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በጽኑ የምትሻው እና የሚያስፈልጋት ጠብመንጃ ያነገቡ የጥፋት ኃይሎችን ሳይሆን፣ በሐሳብ ብስለት፣ በእውነት፣ በዕውቀት እና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን ነው።

ስለሆነም ከዚሁ መሠረታዊ ሐሳብ በመነሣት የታሪክ አጋጣሚዎች እና የዓለማችን ተሞክሮዎች እንደሚያስረዱት በብረት ኃይል የሚመጣ ስኬት ጊዜያዊ እና ሀገርን ወደ ከፋ ውድመት የሚያስገባ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም።

የጠብመንጃ መንገድ የጥላቻ እና የጥፋት አዙሪትን ከማንገሥ ባለፈ የማኅበረሰብ እሴቶችን የሚያፈርስ ሲሆን በሐሳብ ብስለት እና በዕውቀት የታጠቁ የሰላም ታጋዮች ግን የተለያዩ አመለካከቶችን አቃፊ በሆነ መንገድ በማስተናገድ የሕዝቦችን የጋራ የወደፊት ዕድል በጽኑ መሠረት ላይ ይገነባሉ።

በእውነት እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምክክር ለዘመናት የዘለቁ ሀገራዊ አለመግባባቶችን እና ስብራቶችን የመጠገን ከፍተኛ አቅም አለው።

እውነተኛ የሰላም ታጋይነት ሀገራዊ እውነታዎችን በግልጽነት ለመቀበል፣ ታሪካዊ ጠባሳዎችን በጥበብ ለማከም እና የልዩነቶችን ምንጭ በጥልቅ ዕውቀት መርምሮ ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ ያስችላል።

ይህም ሀገራዊ ምክክሩ ከይስሙላ የፖለቲካ ድርድር አልፎ የሕዝቦችን እውነተኛ አንድነት የሚያመጣ የታሪክ ምዕራፍ እንዲሆን ያደርገዋል።

የውይይት እና የእርቅ መንገድ ከግጭት በተቃራኒ የረጅም ጊዜ ትዕግሥትን፣ የሐሳብ ልዕልናን እና የመደማመጥ ባህልን ይጠይቃል።

በመሆኑም የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች እና መላው ሕዝብ በጠብመንጃ ቦታ የሐሳብ የበላይነት እንዲነግሥ በማድረግ ረገድ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር በሐሳብ ብስለት እና በዕውቀት የተዘጋጁ የሰላም ታጋዮች ሀገራቸውን የሚታደጉበት ታላቅ መድረክ ነው።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: