የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዛሬ በተጀመረው 49ኛው የአፍሪካ ሕብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ጂኦ ፖለቲካ አፍሪካ ስትራቴጂካዊ ተዋናይ መሆን እንዳለባት ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን የተመለከቱ ነጥቦችን ባነሱበት ንግግራቸው፣ ጉባኤው የዓለም አቀፍ ሥርዓትና የጂኦፖለቲካዊ አወቃቀሮች ጥልቅ ለውጥ እየታየባቸው ባሉበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑን አመልክተዋል።
የጂኦፖለቲካ ውድድር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች እንዲሁም ስልታዊ በሆኑ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ላይ እየተካሄደ ያለው ውድድር አዲስ የዓለም አቀፍ ሥርዓት እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለዓለም አቀፍ ፈተናዎች አፍሪካውያን መፍትሔዎችን ማቅረብ የምትችል ስትራቴጂካዊ ተዋናይ መሆን እንዳለባት አሳስበዋል።
አፍሪካ ሕብረት የአህጉሪቷን ቅድመ-አጀንዳዎች የሚያስፈጽም፣ መብቷን የሚያስከብርና ተስፋ ሰጪ ድምፅ ሆኖ መውጣት እንዳለበትም ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
አህጉሪቷ እ.ኤ.አ. በ2026 ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ የዓለም 10 ሀገራት መካከል ስምንቱን ያቀፈች በመሆኗ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ሞተር እንደምትሆን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት አህጉራዊ አንድነትና ጥንካሬ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጠዋል።
ሕብረቱ ውሳኔዎቹን በተግባር ለመተርጎም የሚያስችለውን የራሱን ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ማረጋገጥ፣ የጋራ ሀብቶችን በትብብር፣ በፍትሃዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ለአህጉራዊ ትስስርና ብልጽግና ማዋል፣ ችግሮችንም በአፍሪካውያን ተቋማትና ማዕቀፎች መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: