Search

በ45.7 ቢሊዮን ብር በጀት ወደ አዲስ የልማት ምዕራፍ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2019 በጀቱን አጸደቀ

ማክሰኞ ሐምሌ 21, 2018 42

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር 5ኛ የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባዔው በሁለተኛ ቀን ውሎው ለ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚሆን 45.7 ቢሊዮን ብር በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

በጉባዔው ላይ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመሰገን ከበደ በበጀት ዝርዝሩ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በምክር ቤቱ የበጀት፣ ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የኋላእሸት በላይነህ አቅራቢነት ነው በጀቱ የጸደቀው።

የምክር ቤቱ አባላትም የቀረቡትን የዕቅድና የበጀት ሰነዶች መሠረት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ አግኝተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችና እድገቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በየደረጃው የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ትኩረት ከሚያደርግባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የግብርና ግብዓቶችን በጥራት በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋፋት፣ እንዲሁም የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን፣ የሞዴል ገጠር መንገዶችን እና የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማትን ማጠናቀቅ በዋናነት ይገኙበታል።

ከዚህም በተጨማሪ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር፣ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ፓኬጆችን በተግባር ማዋል፣ የህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን መግታት እና የክልሉን የውስጥ ገቢ አቅም አሟጥጦ መሰብሰብ በቀጣዩ ዓመት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ የልማት ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

በሰለሞን ባረና

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: