Search

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አዲሱ የዓለም ሥርዓት፡- የብሪክስ ጥረት እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ዕድል

ማክሰኞ ሐምሌ 21, 2018 33

"የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሀገራትን ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ህይወት በሚለውጥበት በዚህ ዘመን፣ ዋናው ጥያቄ ‘ሰው ሰራሽ አስተውሎት ምን መሥራት ይችላል?’ የሚለው ሳይሆን፣ ‘የቴክኖሎጂውን መጻኢ ዕድል ማን ይቀርጻል? ጥቅሙስ ለማን ይደርሳል?’ የሚለው ነው!"

የብሪክስ አባል ሀገራት ለዚህ ጥያቄ ግልጽ ምላሽ አስቀምጠዋል። ዓለም አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የበላይነትና ደንብ የጥቂቶች ፍላጎት ሳይሆን፣ የሁሉንም ሀገራት ፍላጎት ያማከለ መሆን አለበት። የደቡብ ዓለም ድምጽ እየጎላ የመጣበት ይህ አዲስ የጂኦፖለቲካዊና የቴክኖሎጂ ምዕራፍ፣ ኢትዮጵያም በዲጂታል ዘርፍ አህጉራዊ መሪነቷን የምታረጋግጥበት ታሪካዊ ዕድል ፈጥሮላታል።

በብሪክስ ማዕቀፍ ስር የተያዘው “ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለበጎ ተግባር” የሚለው መርህ፣ የቴክኖሎጂ እድገት በሰው ልጅ ደኅንነት፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሀገራት ዲጂታል ሉዓላዊነት ላይ እንዲመሰረት ያደርጋል። ይህንኑ መርህ በማጠናከር በኩል ቻይና ያቀረበችው ዓለም አቀፍ መመሪያ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሙሉ ድምፅ የፀደቀው የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም ግንባታ ውሳኔ፣ ቴክኖሎጂን ከልማት ጋር በቀጥታ ያያያዘውን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ባጸደቀው መግለጫ መሠረትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር አካታች፣ ልማት ተኮር፣ ተዳራሽ እና የዲጂታል ሉዓላዊነትን የሚያከብር እንዲሆን ተወስኗል። ይህም ቴክኖሎጂው የጥቂት ሀገራት ወይም የላቁ አካላት የበላይነት ማረጋገጫ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ፣ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በኩል መሠረታዊ የቴክኖሎጂ አቅም እንዲገነባ የሚያስችል ፍትሃዊ ተዳራሽነትን ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ከመሆኗ ባሻገር፣ በዘርፉ ለመጠቀም እና የራሷን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ቀደማይ እና አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምራለች። ሀገራችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በሥራ ላይ ለማዋል እና ስጋቶቹን ለመቀነስ የሚያስችል በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ አህጉራዊ አቅኚ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ቀርጻ በመተግበር ላይ ትገኛለች።

በሌላ በኩል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሀገር በቀል አቅም ምርምሮችን በማካሄድ፣ በጤና፣ በግብርና፣ በፋይናንስ እና በቋንቋ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማምረት ረገድ አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

እነዚህ ሀገራዊ ጥረቶች እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ፣ ሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚዋን ለመገንባትና የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ክህሎት ለማሳደግ ከያዘችው እቅድ ባሻገር ከብሪክስ የዓለም አቀፍ ትብብር ጥረት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣሙ ናቸው።

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ትስስር እና ከቴክኖሎጂው ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እንድትጠቀም በርካታ ስትራቴጂያዊ በሮች ተከፍተውላታል። ለአብነትም ቻይና እና ብራዚል ለአነስተኛ አራሾች ያዘጋጁትን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ የቡና እና የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም ይቻላል።

በተመሳሳይ አብዛኞቹ የምዕራባውያን ቴክኖሎጂዎች በውጭ ቋንቋዎች ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ከብሪክስ ሀገራት ጋር በመተባበር በአማርኛ እና በሌሎች ሀገር በቀል ቋንቋዎች የሚሠሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎችን በማልማት ባህልና ቋንቋዋን መጠበቅ ይኖርባታል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያላትን ከፍተኛ አቅም በመጠቀም፣ ለብሪክስ ሀገራት የመረጃ ማዕከላት እና የኮምፒዩቲንግ አገልግሎት ማዕከል ሆና የመቅረብ ትልቅ ዕድል አላት። እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ዋናው ነጥብ፣ የባሕር በርና የሎጂስቲክስ ነፃነትን የሚያረጋግጠው ፊዚካል ሉዓላዊነት እና የቴክኖሎጂ ነፃነትን የሚያረጋግጠው ዲጂታል ሉዓላዊነት የማይለያዩ የሀገር እድገት አምዶች መሆናቸው ነው።

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የምታመርታቸውን የቴክኖሎጂና የዲጂታል አገልግሎት ውጤቶች ያለ አንዳች ገደብ ለዓለም ገበያ ለማቅረብና የሎጂስቲክስ ወጪዋን ለመቀነስ፣ አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘቷ የቴክኖሎጂ አብዮቷን ሙሉ እና ፍሬያማ ያደርገዋል።

ስለሆነም፣ የብሪክስ አካታች የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር አቀራረብ፣ የቴክኖሎጂ እድገት የጥቂቶች ሀብታም ሀገራት መጫወቻ ከመሆን ይልቅ፣ የሁሉንም ሀገራት እድገት የሚያፋጥን የጋራ ዓለም አቀፍ ሀብት እንዲሆን መንገድ ከፍቷል።

ኢትዮጵያ ይህንን እድል በመጠቀም ሀገር በቀል አቅሟን በማጎልበት፣ የዜጎቿን የህይወት ደረጃ ለማሻሻል፣ የኢኮኖሚ ጥገኝነትን ለማስወገድ እና በዲጂታል ዘርፍ የአፍሪካ መሪነቷን ለማረጋገጥ ታሪካዊ እድል በእጇ ላይ ይገኛል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: