በትግራይ ክልል በአሁኑ ሰዓት የህወሓት አፋኝ ቡድን የሥልጣን ጥማቱን ለማርካት ሲል ሕዝቡንና ወጣቱን በኃይል እያስገደደ እንደሚገኝ ከኢቲቪ ትግርኛ ጋር ቆይታ የነበራቸው የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች ገለጹ።
የፖለቲካ ሽንፈትና ድርቀት የገጠመው አፋኙ የህወሓት ቡድን የትግራይን ወጣት በዱላ እየደበደበ በግድ ወደ ማሰልጠኛ ካምፖች እየማገደው ይገኛል ሲሉ ወጣቶቹ በምሬት ሐሳባቸውን ይገልጻሉ። ይህ የጭካኔ ተግባራቸው የሚያሳየው የፖለቲካ ውድቀታቸውንና ሽንፈታቸውን መሆኑንም በአጽንዖት ይናገራሉ።
ከኋላቀር አስተሳሰቡ የማይላቀቀው የህወሓት አንጃ፣ ለትግራይ ሕዝብ እከሌ ጠላትህ ነው፣ በዚህ ሊወርህ እየመጣ ነው እያለ እያሸበረ የመጣ ስብስብ ነው ይላሉ።
አሁን ደግሞ ይህ አልበቃ ብሎት ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ ተጋሩ በሰላም እንዳይኖሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያጠፋህ ነው፣ ሊያስርህ ነው እያለ የተሳሳተ መረጃ እያሰራጨ እንደሚገኝ ወጣቶቹ አጋልጠዋል።
ወጣቶቹ እንደሚሉት፣ የአእምሮ ድርቀት የገጠመው ይህ ቡድን ከዚህ በፊትም ወደ ሥልጣን የመጣው በጦርነት ስለሆነ፣ በዴሞክራሲና በሰለጠነ መንገድ መጓዝ አይችልም።
ስለ ለውጥ ማሰብ የማይችለው ቡድኑ፣ ወጣቶችን እያፈነ፣ እየገደለና እያፈሰ ወደ ጦርነት እያስገባ ይገኛል። ይህ ተግባር ደግሞ ለጨፍጫፊው የህወሓት ቡድን አዲስ ነገር ሳይሆን አብሮት ያደገ ባሕሪው መሆኑን ያብራራሉ።
በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ወጣቶች ከዚህ በፊት በነበረው ጦርነት በተሳሳተ መንገድ የከፈሉት ዋጋ ስለገባቸው፣ አሁን ለአንድ ለከሰረ የህወሓት ቡድን ተጨማሪ ዋጋ መክፈል እንደማይፈልጉና የእምቢታ ድምፅ እያሰሙ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
የትግራይ ሕዝብ በቻለው አቅም የፖለቲካ ውድቀት ያጋጠመውን ይህን ስብስብ አንፈልግም እያለ በመቃወም ላይ ይገኛል። የትግራይ ሕዝብ ያለው ችግርም በሰላም እንዲፈታ የሚፈልግ እንጂ በጦርነት እንደማያምን ያስረዳሉ።
ቡድኑ ማድረግና መፈጸም የማይችለውን ነገር እያነሳ ሕዝቡን ወደ ተሳሳተ መንገድ ለማስገባት ቢሞክርም፣ ወጣቱ በተግባር እምቢተኝነቱን እያሳየ ይገኛል። ለለውጥ ዝግጁ ያልሆነው ይህ አንጃ የትግራይን ወጣት በምንም ተአምር ሊያሻግረው አይችልም።
የአንድ ቤተሰብ ስብስብ የሆነው የህወሓት ቡድን ከጅምሩ አንስቶ ለመላው የትግራይ ሕዝብ ጥቅም የታገለ ፓርቲ አለመሆኑን ሕዝቡ በደንብ ያውቃል ሲሉ ወጣቶቹ በአጽንዖት ገልጸዋል።
ሕዝቡ በኃይልና በአፈሙዝ ስለተጨቆነ ነው እንጂ ቡድኑ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደማያመጣለት ጠንቅቆ ተረድቷል። የህወሓት ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ቢታገል ኖሮ፣ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን ሕዝብ በ1983 ዓ.ም ለሁለት የከፈለ፣ ትግራይን በጂኦግራፊ ከበባ ውስጥ ያስገባ እና የሐሳብ የበላይነት የተወሰደበት የማይማርና የማይቀየር ስብስብ አይሆንም ነበር በማለት ገልጸውታል።
አባቶቻችን ሲገለገሉበትና ሲያስተዳድሩት የነበረውን የቀይ ባሕር ወደባችንን አሳልፎ በመስጠት ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር መፈጸሙንም ያስታውሳሉ።
የፖለቲካ ቀውስ የገጠመው የህወሓት ቡድን ሀገር እንዳትረጋጋ የሚያሴረው ሴራ አልበቃም ብሎት፣ አሁን ደግሞ የፕሪቶሪያው ስምምነት ለምን ተፈረመ ከሚሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር "ፅምዶ" (ትብብር) በሚል ሀገርን ለማፍረስ ቀንና ሌሊት እየሠራ ይገኛል ሲሉ በምሬት ይገልጻሉ።
"ፅምዶ" ብለው የፈጠሩት ትብብር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚቃረን፣ ተጋሩን ለውድቀት የሚዳርግና የሻዕቢያን ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው በማለት ያጋልጣሉ። ይህ ከስህተቱ የማይማር ቡድን ሀገራችንን ለማፍረስ የሚያደርገውን ሴራ ለማክሸፍ ሀገርን ለማጽናትና ለማስቀጠል ከፌዴራል መንግሥት ጎን ሆነን እንታገላቸዋለን ብለዋል እነዚህ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች።
የፖለቲካ ቀውስ የገጠመው የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና ሰቆቃ ሁሉም ወገን ሊታገለው እንደሚገባ በመግለጽ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ሀገራችን ሰላም እንዳታገኝና እንድትበታተን ከውስጥና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር እየሠራ ያለውን ይህን አክራሪ ቡድን ከፌደራል መንግሥት ጎን በመቆም እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንታገለው ይገባል ሲሉ ወጣቶቹ በአጽንዖት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጎሳዬ ገ/ኪዳን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: