ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ታሪካዊና ጂኦፖለቲካዊ የበላይነት እንድታጣ ያደረጋት የ1983 ዓ.ም የሽግግር ወቅት፣ በሕወሓት እና በሻዕቢያ መካከል በሕጋዊ ሰነድና ድርድር ሳይደገፍ በተፈጸመ ሴራ መሆኑን አንጋፋው ፖለቲከኛ ሌንጮ ለታ ገለጹ።
ከኢቲቪ አዲስ ቀን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መስራችና የቀድሞ አመራር አቶ ሌንጮ ለታ፤ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሴራ ኤርትራ እንድትገነጠል ሲደረግ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ያላገናዘበና በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ውል ያልተደገፈ ውሳኔ መወሰኑን አብራርተዋል።
በዚህም ምክንያት የኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት የአሰብን ወደብ ጨምሮ ሙሉ የባሕር ዳርቻውን በፖለቲካ ሴራ እንዲቆጣጠር መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ በሕዝቧና በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ሲሆን፣ ሀገራችን ለውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለወደብ ኪራይ እንድታወጣ አድርጓታል።
ይህም የትራንስፖርት፣ የምግብና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ዋጋ እንዲንር በማድረግ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የተፈተነበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት አንጻርም የባሕር በር ማግኘት የፖለቲካ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አቶ ሌንጮ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የባሕር በር ያሳጣው ውሳኔ በሕዝብ፣ በፓርላማ ወይም በካቢኔ ያልተወሰነና ሕጋዊና መሠረታዊ ሰነድ የሌለው መሆኑን መጠቆማቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሕዝብ ተወካዮችና ካቢኔው ሳያውቁት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ያሳጣው የፖለቲካ ሴራ ውሳኔ እንዴትና በማን ተወሰነ ብሎ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው” ሲሉ መናገራቸውም የሚታወስ ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስከበር የምታደርገው ጥረት ይህን ታሪካዊ ስህተት ለማስተካከልና የሀገራችንን የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚና ደህንነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተመልክቷል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: