Search

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አስተዳደር እና ባለብዙ ወገን ሥርዓቶች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠየቀች

ዓርብ ግንቦት 07, 2018 69

ኢትዮጵያ እኩልነት፣ ሚዛነዊ ውክልና፣ ተቀባይነት ያለው እና ፍትሐዊነት የሰፈነበት የዓለም ሥርዓት ለመገንባት በብሪክስ ቤተሰብ እና በሰፊው ባለብዙ ወገን ሥርዓት ውስጥ አብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን የኢትዮጵያ ልዑክ 2026 የብሪክስ ስብሰባ ላይ ባስተላለፈው መግለጫ አረጋግጧል።

ልዑኩ በማሻሻያዎች እና በነባራዊ ሁኔታዎች ቀጣይነት መካከል ጥንቃቄ የተሞላበት ሚዛን የመጠበቅን አስፈላጊነት ጨምሮ፣ በዋና ዋና የዓለም አቀፍ አስተዳደር እና ባለብዙ ወገን ሥርዓቶች ማሻሻያ ላይ የኢትዮጵያን አቋም አጉልቷል።

በዚህም መሠረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ፣ ኢትዮጵያ በኤዙልዊኒ ስምምነት (Ezulwini Consensus) እና በሲርቴ መግለጫ (Sirte Declaration) ላይ በተደነገገው መሠረት ከአፍሪካ የጋራ አቋም ጎን በፅናት እንደምትቆም ልዑኩ ገልጿል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ውክልና አፈጻጸም እና ዝርዝር አካሄድ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለአህጉሪቱ ራሷ መተው እንዳለበት ልዑካን ቡድኑ በአጽንኦት አሳስቧል።

በፋይናንስ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች ረገድ፣ ልዑኩ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ካለው አንጻራዊ ድርሻ አንጻር የሀገራት የውክልና ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት አስገንዝቧል።

ከኮታ ማስተካከያ ባለፈም፣ የሚደረጉ ማሻሻያዎች የሀገራትን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲኖር ለማረጋገጥ ማገዝ እንዳለባቸው ተገልጿል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ለመደገፍ የዕዳ ሽግሽግ/ማሻሻያ አሠራሮችን በአስቸኳይ ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ልዑካን ቡድኑ ጠቁሟል።

በዓለም የንግድ ድርጅት ማሻሻያን በተመለከተም፣ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን በንቃት እየተደራደረች መሆኑን ልዑኩ ጠቅሷል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአባልነት ሂደቱን በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያገናዝብ አድርጎ እንዲያሻሽልም ጥሪ አቅርቧል።

ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የክርክር መፍቻ ሥርዓቱን ማጠናከር እንዲሁም ያላደጉ ሀገራት በአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ስም ከሚጣሉ እና በረቀቀ መንገድ ከሚተገበሩ የንግድ ገደቦች ሊጠበቁ እንደሚገባ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከግንቦት 6 እስከ 7 ቀን 2018 . በኒው ዴልሂ፣ ሕንድ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በመሳተፍ ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።