Search

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከሳዑዲ የልማት ፈንድ አመራሮች ጋር ተወያየ

ሓሙስ ሚያዝያ 08, 2018 84

በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን፣ በዋሽንግተን ዲ.ሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የፀደይ ስብሰባ ጎን ለጎን ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱልጣን አብዱልራህማን አል-ማርሻድ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርጓል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ያለውን ጠንካራ እና እያደገ የመጣ አጋርነት አድንቀዋል።

ሚኒስትሩ መንግሥት እያከናወነው ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ የሚሹ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎችንም ዘርዝረዋል።

የውይይቱ ዋና ዋና ነጥቦች ስትራቴጂያዊ በሆኑ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በተለይም ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሊደረግ በሚችል የፋይናንስ ድጋፍ ዙሪያ ያተኮሩ ነበሩ።

የኢኮኖሚ ዕድገትን እና ቀጣናዊ ትሥሥርን ለመደገፍ የመንገዶች ትሥሥርን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም መክረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው የልማት ኢኒሼቲቮችን ለማሳካት ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

የሳዑዲ የልማት ፈንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱልጣን አብዱልራህማን አል-ማርሻድ በበኩላቸው፣ የሳዑዲ የልማት ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት አረጋግጠው፣ የሀገሪቱን ዋና ዋና የልማት ተነሳሽነቶች ለመደገፍ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

#EBC #Ethiopia #SDF #diplomacy