ኢትዮጵያ በታሪኳ ለዘመናት ከባሕር ጋር የነበራት ቁርኝት ከጂኦግራፊያዊ መሳ ለመሳነት በዘለለ የሀገራችን የሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ጥንካሬ እና የቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መሠረት ሆኖ ኖሯል።
በጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ወቅት የአዱሊስ ወደብ የዓለም የንግድ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል፣ ኢትዮጵያውያን እ.ኤ.አ በ518 ወደ የመን ባሕር ተሻግረው ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ከ70 በላይ የጦር መርከቦችን በአገር ውስጥ የመገንባት ጥበብ ነበራቸው። ይህ ጥንታዊ የባሕር ግርማ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦቶማን ቱርኮች ምጽዋን እስከተቆጣጠሩበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያን የባሕር ሉዓላዊነት ሲያስከብር ቆይቷል።
የባሕር ኃይሉ መሥራችና ታሪካዊው ምዕራፍ
በዘመናዊው የሀገራችን ታሪክ ደግሞ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1948 ዓ.ም የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል እንደ አዲስ ሲያቋቁሙ፣ ዓላማቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ ያላትን ድርሻ ለማስከበር እና የቀይ ባሕር ዳርቻዋን ከማንኛውም ወረራ ለመጠበቅ ነበር።
በወቅቱ የምጽዋው የባሕር ኃይል ጣቢያ የቀጣናው የጥንካሬ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ በየዓመቱ ጥር ወር ላይ የሚከበረው የባሕር ኃይል ቀን የዓለም ኃያላን ሀገራት ሳይቀሩ የጦር መርከቦቻቸውን በመላክ ለኢትዮጵያ ክብር የሚሰጡበት ታላቅ ወታደራዊ ክስተት ነበር። የባሕር ኃይሉ ባንዲራ ተሸካሚ የነበረችው "ኤትዮጵያ" መርከብም ለሦስት አሥርተ ዓመታት የሀገራችን ኩራትና የባሕር ላይ ልምምድ ማዕከል ሆና አገልግላለች።
ይሁን እንጂ በ1983 ዓ.ም በሀገር ውስጥ በነበረው የፖለቲካ ለውጥ እና በተካሄደው ኢትዮጵያን ከኖረችበት ቀይ ባሕር የማራቅ ሴራ ምክንያት ኢትዮጵያ ለዘመናት የገነባችውን የባሕር ኃይል ንብረትና መሠረተ ልማት በአንድ ጀንበር ለማጣት ተገድዳለች። በወቅቱ በርካታ መርከቦች እንዲወድሙ ሲደረግ፣ ሌሎች ወደ የመንና ሳዑዲ ዓረቢያ ሄደዋል። ገሚሱም በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ቀርተዋል።
ቀጥለው በመጡት ዓመታት ሀገራችን በ"ጂኦግራፊያዊ እስር ቤት" ውስጥ እንድትቆይ ተደርጎ የቆየ ሲሆን፣ በ1988 ዓ.ም የባሕር ኃይሉ በይፋ እንዲፈርስ መደረጉ የኢትዮጵያን የባሕር ሉዓላዊነት አዳክሞት ቆይቷል። ይህ ወቅት ኢትዮጵያ በወደብ አገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ደኅንነት ረገድም በሌሎች ሀገራት በጎ ፈቃድ ላይ እንድትደገፍ ያስገደዳትን የታሪክ ጠባሳ የፈጠረ ነበር።
የዳግም ትንሣኤ ጉዞ እና ተቋማዊ ግንባታ
ይህ የታሪክ ሂደት በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ያለ ባሕር በር መኖር አትችልም" በሚል የጀመሩት ብሔራዊ ጥሪ ኢትዮጵያን ከባሕር ነጥሎ ማቆየት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ለዓለም ያሳየ ተግባራዊ እርምጃ ነው።
በ2011 ዓ.ም የባሕር ኃይሉን እንደ አዲስ የማደራጀት ዕቅድ ይፋ መደረጉ፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ደኅንነት ለማረጋገጥ እና ታሪካዊ ክብሯን ለመመለስ የተወሰደ ብርቱ ውሳኔ ነበር።
በዚህ የዳግም ትንሣኤ ጉዞ ውስጥ በአጭር ጊዜ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በቢሾፍቱ ከተማ በመርከብ ቅርጽ ተገንብቶ በጳጉሜ 2017 ዓ.ም በይፋ የተመረቀው ዘመናዊ የባሕር ኃይል ሥልጠና ማዕከል ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል አባላቶቿን በራሷ መሐንዲሶችና ባለሙያዎች ለማሰልጠን ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ በ2 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ባለ 4 ወለል ዘመናዊ የባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታው በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ላይ 95 በመቶ መድረሱ፣ ተቋሙን በዘመናዊ የስትራቴጂካዊ አመራርና ቴክኖሎጂ ለማደራጀት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያረጋግጣል።
የስትራቴጂካዊ ተቋማት ደኅንነት እና የባሕር ሎጂስቲክስ አቅም
የባሕር ኃይሉ ዳግም መደራጀት ከባሕር ዳርቻ ባለፈ፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ስትራቴጂካዊ ተቋማትን በመጠበቅ ረገድም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ የተፈጠረውን ግዙፍ ሰው ሠራሽ ሐይቅና አካባቢውን ለመጠበቅ የተቋቋመው የባሕር ፖሊስ ኃይል፣ የግድቡን ደኅንነት ከማንኛውም የጥፋት ሙከራ ለመከላከል በዘመናዊ ጀልባዎችና ራዳሮች ታጥቆ ወደ ሥራ ገብቷል። ይህ ኃይል የግድቡን የውኃ አካል ለሀገራዊ ኢኮኖሚና ለሰላም ዋስትና እንዲውል የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
የኢትዮጵያ የባሕር ኃያልነት የሚረጋገጠው በውታደራዊ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በንግድ መርከቦች አቅም ግንባታም ጭምር ነው። በ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 6 አዳዲስ የጭነት መርከቦችን ለመግዛት መወሰኑ፣ የሀገራችንን የውጭ ንግድ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተወሰደ እርምጃ ነው።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መርከቦች በቀይ ባሕር ቀጣና ያለውን የጸጥታ ሥጋት ተቋቁመው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ወደብ ባይኖራትም በባሕር ላይ ያላት ተጽዕኖ ፈጽሞ ሊገታ እንደማይችል ለዓለም ያስመሰከረችበት ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል "ከትናንት እስከ ዛሬ" ያደረገው ጉዞ የታሪክ ክብርን የመመለስና የወደፊት ሕልውናን የማረጋገጥ ሂደት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጀመሩት ይህ ታላቅ ስትራቴጂካዊ ተልዕኮ፣ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ እንደገና የባሕር ኃያል ሀገር እንድትሆን የማድረግ ግልጽ ራእይ አለው።
በየካቲት 2018 ዓ.ም ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙን ጨምሮ ለበርካታ የባሕር ኃይል መኮንኖች የተሰጠው የማዕረግ ዕድገትም፣ የባሕር ኃይሉን ተቋማዊ ዝግጁነትና ብቃት ይበልጥ አጠናክሮታል። ኢትዮጵያን ከባሕር ነጥሎ ማቆየት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን በተግባር ያሳዩት እነዚህ እርምጃዎች፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ የሉዓላዊነት አሻራ ሆነው ይመዘገባሉ።