Search

ሀገር በጦር ሳይሆን፣ በመደማመጥ ትፀናለች፡- ቅሬታዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመዝጋት አዲስ ምዕራፍ

ማክሰኞ ሐምሌ 21, 2018 52

ትናንት ሀገርን ለማፅናትና ዳር ድንበሯን ለማስከበር መሳሪያ አንግበው ለሀገራችን ሉዓላዊነት በተለያየ ዘመን የተዋደቁ የሠራዊት መኮንኖች፣ ዛሬ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል። በፖለቲካ አመለካከት ልዩነታቸው የከረረ አቋም የያዙ የፖለቲካ ኃይሎችም የፓርቲ ፍላጎታቸውን ወደ ጎን አድርገው በአንድ አዳራሽ ተሰባስበዋል። ይህም የአንድ አካል ታሪክ አይደለም፤ የነገዋ ኢትዮጵያ የጋራ መግባባት ሰነድ መሆኑን ነው የሚያሳየው።

እንደ ሀገር እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መድረኩ ከታች ወደ ላይ የመጣና ሕዝባዊ መሠረት ያለው ሲሆን፣ የምክክሩ አጀንዳዎችም ከወረዳ ጀምሮ የዜጎችን ብሶት፣ ጥያቄና ተስፋ ያካተቱ ናቸው።

አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት፣ የሠለጠነ የፖለቲካ ባህልን የሚያጎለብተው ምክክሩ፣ ሐሳብን በሐሳብ የማሸነፍ ነፃ መድረክ ሲሆን፣ የፖለቲካ ኃይሎች የፓርቲ አጀንዳቸውን አስቀርተው ለሀገር የጋራ ኅልውና በአንድነት የቆሙበት ከፖለቲካ በላይ የሆነች ሀገር የመገንባት ሂደትም ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የጀግንነት ድሎችንና የጥንካሬ ማረጋገጫዎችን እንዳስመዘገበች ሁሉ፣ ፈታኝ የሚባሉ አጋጣሚዎችንም አሳልፋለች። ለዘመናት ያልተፈቱ የፖለቲካ ችግሮች፣ የታሪክ ቅሬታዎችና የፍትሕ ጉድለቶች በሕዝቦች መካከል እንደ ትልቅ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸው አይዘነጋም። ሆኖም ኢትዮጵያውያን ከጥንት አያት ቅድመ አያቶቻቸው የካበቱት ታላቅ ጥበብ ቢኖር፣ አለመግባባቶችን ከዋርካው ሥር በውይይትና በሽምግልና የመፍታት እሴት ነው።

ዛሬ ደግሞ ያንን የቅሬታና የቁስል ምዕራፍ በቃ ብሎ የመዝጊያው ጊዜ ላይ ደርሷል። “አጀንዳችሁ ሀገርን ያቀናል፤ ብንመክርበት ለመግባባት መንገዳችን ይበጃል” በሚል እምነት ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሁሩ እስከ ገበሬው፣ ከመሻይኹ እስከ ቀሳውስቱ ያሉ ተመካካሪዎችን በማሰባሰብ ታሪካዊ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ይህ መድረክ ከላይ የተጫነ ውሳኔ ሳይሆን፣ መነሻውን ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ያደረገ ሕዝባዊ ሂደት ነው። ከወረዳ ጀምሮ የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር፣ እያንዳንዱ ዜጋ የችግሩ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ የመፍትሔውም አካል መሆኑን አረጋግጧል።

በተለይም በዲሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ ልዩነቶች የሀገርን ኅልውና ሲነኩ ግን መድኃኒቱ ፉክክር ሳይሆን ውይይት ነው። ለዚህም ነው የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የግልና የፓርቲ ፍላጎታቸውን ወደ ጎን ትተው የሀገርን ጥቅም በማስቀደም በአንድ አዳራሽ የተሰባሰቡት። ይህ እርምጃ "ሀገር ስትጠራ የፖለቲካ ፍላጎት ወደ ኋላ ይቀራል፤ የጋራ ሀገራዊ ኃላፊነት ግን ወደ ፊት ይመጣል" የሚለውን ወርቃማ እውነት ያስመሰከረ ነው።

ሀገር በአንድ ቀን እንዳልተገነባች ሁሉ፣ ያሉባትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታትም ትዕግሥት፣ ሂደትና የጋራ ጥረት ያስፈልጋል። ይህ የምክክር ሂደት የአንድ ወገን አሸናፊነት የሚረጋገጥበት ሳይሆን፣ የመደማመጥ፣ የመተማመን እና የጋራ መፍትሔ ፍለጋ መድረክ ነው። ዛሬ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚሰሙ ድምፆች፣ ነገ በአንድነት የምትቆም፣ የጸናችና የሁሉም ድምፅ የተከበረባትን ኢትዮጵያ የሚያንጹ መሠረቶች ናቸው።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: