Search

የታሪክ ሴራዎችን ያከሸፈው የፍትሓዊነት ማረጋገጫ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

ማክሰኞ ሐምሌ 21, 2018 67

የኢትዮጵያውያን ዳግማዊ ዓድዋ የሆነው ታላቁ  የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘመናትን የተሻገሩ ውጫዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ሴራዎችን በስልታዊ ዲፕሎማሲ በመበጣጠስ እና ውስጣዊ የግንባታ መጓተቶችን በህዝብ የተባበረ ክንድ በመሰባበር በታላቅ ስኬት ተጠናቋል።

በኢትዮጵያውያን ደም፣ ላብና ቁጠባ የተገነባው ይህ ታላቅ ፕሮጀክት፣ ለመላው ሕዝብ ትልቅ ብስራትና የጋራ ደስታን ያበሰረ፣ የዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬያችንንም ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ አልፏል።

በዚህ ረጅም ታሪካዊ ሂደት የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ እንዳይነቁና ተፈጥሯዊ ሀብታቸውን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ በርካታ የማደናቀፍ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ግድቡም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር እንዳይሰጡ ከመጎትጎት ጀምሮ በጉዳዩ ቀጣናዊ ውጥረቶችን ለመፍጠር ሞክረዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን አቅምና የህዝቦቿን ጽናት ካለመገንዘብ የመነጨው የጠላቶች ትዕቢት ሳይሳካ ቀርቷል። በብሔራዊ ጥቅማቸው የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን ግድቡ የኔ ነው በሚል መፈክር በአንድነት በመነሳት ገንዘብ ጉልበት ሀሳብና ጊዜያቸውን በመስጠት ፈተናውን ወደ ትልቅ የልማት ዕድል ቀይረውታል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊና ሕጋዊ የመጠቀም መብት በጽናት ያስከበረች እና ግብፅ የዓባይን ወንዝ በኢ ፍትሐዊ መንገድ ለዘመናት በብቸኝነት የማቀብ ፍላጎቷን በመረጃና በማስረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጋልጣለች።

በተጨማሪም ከላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር በመተባበር የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማርቀቅና በማጽደቅ የጠላቶችን በብቸኝነት የመጠቀም ታሪክ ማክተም ችላለች።

በሳይንሳዊ ማስረጃዎችና ድንበር ተሻጋሪ የወንዞች ሕግ መሠረት ግድቡ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስ ያረጋገጠችው ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትና የቀጣናዊ ትስስር ራዕይ መርህን በመከተል የጠላቶችን የስጋት ፕሮፖጋንዳ በተግባር አፍርሳዋለች።

የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት ጥበብን የተከተለና ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በተግባር በማዋል ረገድ ያላትን የመሪነት ሚና ዳግም ያረጋገጠ ስልታዊ ድል ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ መጠናቀቅ ሀገራችን በዓለም መድረክ አዲስ የጂኦፖለቲካና የኢኮኖሚ ግርማ ሞገስ በማልበስ የምስራቅ አፍሪካ ዋነኛ የኃይል ማዕከል ያደረጋት ታላቅ ድል ነው።

እንዲሁም የኢትዮጵያ አቋም አሁንም የጸናና የማይናወጥ ሲሆን ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብት ለአፍታም ቢሆን ለድርድር እንደማታቀርብ አረጋግጣለች።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሀብትን በብቸኝነት የመጠቀም ጊዜ አብቅቶ ከመገፋፋት ይልቅ በትብብር አብሮ የማደግና የማልማት አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ያደረገ የዘመናችን ትልቅ ስኬት ነው።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: