Search

መድዓ፡ ዘመናትን የተሻገረው ሀገር በቀል የፍትሕ ሥርዓት

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 53

ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ህልውናዋን፣ አብሮነቷን እና ሰላሟን ጠብቀው ያቆዩ በርካታ ሀገር በቀል ባህላዊ እሴቶች እና የዕውቀት ሥርዓቶች ባለቤት ናት። ከእነዚህ ደማቅ እሴቶች መካከል ደግሞ የማኅበረሰቡን መረጋጋት ሲያረጋግጥ የኖረው ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

በአፋር ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት ዘላቂ ሰላምን፣ ማኅበራዊ ደኅንነትን እና ሥርዓትን ሲያስጠብቅ የኖረው "መድዓ" የተሰኘው ባህላዊ የሕግ እና የፍትሕ ሥርዓት አንዱ የዚህ ሀገር በቀል እሴት ማሳያ ነው።

መድዓ በአፋር ማኅበረሰብ ዘንድ የግለሰቦችን፣ የቤተሰብን እና የጎሣዎችን ድንበሮች መብቶች እና ግዴታዎች የሚወስን፣ ግጭቶችን የሚያስወግድ እና ጥፋተኞችን በይቅርታ የሚያርም ድንቅ የማኅበራዊ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ነው።

 

በታሪካዊ ጥናቶች መሠረት የመጀመሪያው መድዓ የተቀረጸው ከሦስት መቶ አርባ ዓመታት ገደማ በፊት ነው። ዋና ዓላማውም በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ መካከል የጋራ መግባባትን መፍጠር እና በሀብት፣ በተለይም በግጦሽ እና በውኃ ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን መቆጣጠር ነበር።

መድዓ በአፈ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ያልተጻፈ የሕግ አካል ቢሆንም፣ በዘመናዊ የሕግ መርሆች የሚታወቀውን "የመንግሥት የሥልጣን ክፍፍል" መርሕ በራሱ መንገድ በተግባር ያዋለ የተከበረ ተቋም ነው። ሥርዓቱ የራሱ የሆነ የሕግ አውጪ፣ የሕግ ተርጓሚ (ዳኝነት) እና የሕግ አስፈጻሚ አካላት አሉት።

በተለይም "ማሮ" በተሰኘው በዛፍ ስር በሚካሄደው ባሕላዊ የችሎት መድረክ፣ ዳኞች ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ውሳኔውን የማስፈጸም ጥፋተኞችን የመያዝ እና የሕዝቡን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የሚወድቀው "ፊማ" በተሰኘው ጠንካራ የወጣቶች ማኅበር ትከሻ ላይ ነው።

ሥርዓቱ ጥፋቶችን በአምስት ክፍሎች ማለትም በሕይወት ላይ የሚፈጸም፣ በአካል ላይ የሚፈጸም፣ በንብረት ላይ የሚፈጸም፣ ትዳር ጋር የተያያዘ፣ የስድብ እና ስም ማጥፋት በማለት በመለየት ጥንቃቄ የተሞላበት የምርመራ በማካሄድ ነው ወደ ፍርድ የሚሄዱት።

የመድዓ ጥበብ ዋና ምስጢር ያለው በማስገደድ እና በመቅጣት ላይ ሳይሆን፣ በማገገም ፍትሕ ፍልስፍና ላይ መመሥረቱ ነው። በመድዓ ሕግ መሠረት የወንጀል ተጠያቂነት በጎሳው ላይ ስለሚያርፍ አንድ አባል ጥፋት ሲፈጽም ጎሳው የደም ካሳውን በጋራ አዋጥቶ ይከፍላል። ይህ አሠራር እያንዳንዱ የጎሳ አባል የሌላውን ባሕሪ እንዲቆጣጠር በማድረግ ተፈጥሯዊ የቁጥጥር ሥርዓት ይፈጥራል።

ደጋግሞ ወንጀል የሚፈጽም ግለሰብ ከተገኘ ጎሳው ግለሰቡን ሙሉ በሙሉ ከወገንነት ያገላል። በአርብቶ አደሩ አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ከወገን መገለል የህልውና አደጋ በመሆኑ ይህ ሥርዓት ወንጀልን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ዳኞችም ካሳውን ሲወስኑ እስከ 10 በመቶ ቅናሽ በማድረግ የተበዳይ እና የበዳይ ቤተሰቦችን በማስታረቅ የደም በቀልን ከሥሩ ያስቀራሉ።

ተጨባጭ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የግጭት እና የፍትሕ ጉዳዮች የሚታዩት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ሳይሆን በባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ነው።

መድዓ ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር፣ የጠበቃ እና የፍርድ ቤት ወጪ የማይጠይቅ፣ በዛፍ ስር በግልጽነት የሚካሄድ፣ ታማኝ በሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች የሚመራ እና የጊዜ ብክነትን የሚያስቀር በመሆኑ ከፍተኛ የሕዝብ አመኔታ አግኝቷል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደች ያለችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት እንደ መድዓ ያሉ ዘመናትን የተሻገሩ፣ የበሰሉ እና ማኅበረሰቡ ላይ ዘላቂ በጎ ተፅዕኖ ያሳደሩ ሀገር በቀል ጥበቦችን መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሰላምን ሲያስጠብቅ የኖረው የመድዓ መርሕ ችግሮቻችንን ከመሰረቱ የሚፈታ ነው። መድዓ አሸናፊ እና ተሸናፊን ከሚለየው አሠራር ይልቅ የበዳይ እና የተበዳይ ቤተሰቦችን አቀራርቦ እርቅን የሚፈጥር ነው። በዚህም ማኅበራዊ ሚዛንን በማስቀደም ማኅበረሰባዊ ቁስል ሳይተው ፍትሕን ያሰፍናል።

እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደቱም የፖለቲካ ልዩነቶችን በጋራ መግባባት እና በይቅርታ ለመፍታት ከእንደዚህ ዓይነት ባህላዊ የእርቅ እሴቶቻችን ትልቅ ትምህርት ይወስዳል።

እነዚህን እሴቶች የማኅበራዊ ሀብታችን አካል በማድረግ ሀገራዊ መግባባትን ማጠናከር እና ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስተላለፍ እንችላለን።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: