Search

የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ስንዴ ልማት

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 29

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የማንኛውም ሀገር ሉዓላዊነት፣ ክብር እና ነፃነት መሰረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነችው ያለው የልማት እንቅስቃሴ፣ በተለይም በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት፣ ሀገራዊ ነፃነትን በኢኮኖሚና በምግብ ዋስትና ለማፅናት የተወሰደ ትልቅ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።

በሀገራችን በሰፊው የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አጠቃላይ የግብርና ምርታማነት አስተሳሰብን የቀየረ ክስተት ሆኗል።

ቀደም ሲል በዋናው የዝናብ ወቅት ብቻ ይከናወን የነበረውን አሠራር በመቀየር፣ ሀገራችን ያላትን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በብቃት በመጠቀም ዓመቱን ሙሉ ማረት ተችሏል።

ይህም በየዓመቱ ይደረግ የነበረውን ከፍተኛ የስንዴ ግዢ በማስቀረት እና ከውጭ ገቢ ጥገኝነት በመውጣት ረገድ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል።

ስንዴን በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ማምረት ከውጭ ለመግዛት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማዳኑ ባሻገር በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በሚፈጠሩ የዋጋ መናወጦችና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች የሚመጣን ኢኮኖሚያዊ ጫና ይቀንሳል።

ከዚህም በላይ በምግብ እርዳታ ስም የሚመጡ ውጫዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን በማስቀረት ሀገራችን በሁለት እግሯ እንድትቆም እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በነፃነት እንድትወሰን ያስችላታል።

ሉዓላዊነት የሀገር ድንበርን ከመጠበቅ ባሻገር የሕዝብን የዕለት ጉርስ በራስ አቅም ማቅረብ መቻል ነው።

ለዘመናት በምግብ እርዳታ ትታወቅ የነበረችውን ሀገር ገጽታ በመቀየር፣ በምግብ ራስን መቻል ለዜጎች ኩራት እና ለሀገር ክብር መሰረት ነው።

በስንዴ ምርት የተመዘገበው ውጤት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ምርት ማቅረብ የሚያስችል አቅም እምነት የገነባ ነው፡፡ ይህም በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ያላትን ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ያሳድገዋል።

በስንዴ ልማት የተገኘው ተስፋ ሰጪ ስኬት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቅማ ራሷን መመገብ እንደምትችል በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ይህ የልማት መስመር ተጠናክሮ ሲቀጥል የኢኮኖሚ ጥገኝነትን በማስወገድ እውነተኛውን ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና የነፃነት ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: