Search

የሉዓላዊነት እና በተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት ማረጋገጫ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 36

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶችን፣ የጂኦፖለቲካዊ ጫናዎችን እና የኢኮኖሚ ፈተናዎችን አልፎ፣ ዛሬ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት እና የፅናት ማሳያ መሆን ችሏል።

ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሀገራችንን የኢኮኖሚና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ታሪካዊ ብስራቶችን ይዞልን መጥቷል።

የግድቡ የውኃ ሙሌት ሂደት የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም በማይጎዳ መልኩ በተያዘለት እቅድ መሠረት ደረጃ በደረጃ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ የዘመናችን ትልቁ ስኬት ነው። ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በፍትሃዊነት የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን በተግባር ካረጋገጠችበት ታሪካዊ ሁነቶች አንዱ ነው።

የግድቡ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው ፕሮጀክቱ ከፅንሰ-ሐሳብ እና ከግንባታ ደረጃ አልፎ ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ ጥቅም መሸጋገሩን አብስሯል። በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨቱ ደግሞ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች፣ ለንግድ ተቋማት እና ለዜጎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ ያለምንም የውጭ ብድር እና እርዳታ፣ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን እና በዲያስፖራው የገንዘብ፣ የጉልበት እና የእውቀት አስተዋጽኦ እውን መሆኑ ትልቅ የሞራል እና የዕድገት ማብሰሪያ ነው። ኢትዮጵያውያን በጋራ ሀገራዊ ዓላማ ዙሪያ ከተሰለፉ የማያሳኩት ግብ እንደሌለ ለዓለም ያስመሰከረም ጭምር ነው።

ግድቡ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችለውን አቅም በማሳደጉ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል አድርጓታል። ይህም የሀገራችንን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም ሆኗል።

በተጨማሪም በግድቡ የተፈጠረው ሰፊ ሐይቅ ለዓሣ ሀብት ልማት፣ ለጀልባ ትራንስፖርት እና ለቱሪዝም መስክ አዳዲስ የኢኮኖሚ እድሎችን ይዞ መጥቷል። ይህም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ እድል እና አዲስ የልማት አማራጮችን መፍጠር አስችሏል።

በአጠቃላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን የታላቅነት፣ የመቻቻል፣ የፅናት እና የአንድነት ህያው ምስክር ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: