የአፍሪካን አህጉር በጎና እውነተኛ ገጽታ ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው ትውልደ አዘርባጃኑ ዳዉድ አኹንድዛዳ (Dawood Akhundzada)፣ የኢትዮጵያን መዲና አዲስ አበባን እና ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን ለሚሊዮን ዓለም አቀፍ ተከታዮቹ እያስተዋወቀ ይገኛል።
የፋርማሲ ባለሙያ የነበረው ዳውድ ቦርሳውን በጀርባው አዝሎና ስልኩን ብቻ በመጠቀም በሚያቀርባቸው ሳቢ ቪዲዮዎች፣ አዲስ አበባ የበለጸገ ታሪክና ዘመናዊ እድገት የሚገናኙባት ህያው ከተማ መሆኗን አሳይቷል።
በከተማዋ መንገዶች ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ፣ ከባህላዊ መንደሮች ጎን ለጎን ከሚያንጸባርቁ ፎቆችና አዳዲስ አውራ ጎዳናዎች በተጨማሪ፤ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና ዘመናዊው የቀላል ባቡር አዲስ አበባን የአፍሪካ ዋነኛ ማዕከል እንዳደረጓት ይመሰክራል።
በኮሪደር ልማት ይበልጥ የተዋበችው መዲናችን የሀገር ውስጥ ጣዕምን ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር በሚያዋህዱ ቄንጠኛ ካፌዎች፣ የገበያ ማዕከላት፣ ዘመናዊ የጥበብ ጋለሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞችና ዓለም አቀፍ ሆቴሎች የተሞላች መሆኗን ገልጿል።
ከተማዋ በሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች እየዘመነች ብትሄድም፣ የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓቱና መዓዛው አሁንም ከከተማዋ ባህልና ዘመናዊ ሕይወት ጋር በጥልቅ የተሳሰረ መሆኑን አስገንዝቧል።
ከዚህም ባሻገር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በማቅናት በ12ኛው እና በ13ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላሊበላ ዘመን የተፈለፈሉትን አስራ አንድ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘው ዳውድ፣ ስፍራውን “በዓለም ውስጥ ከሚገኙት በጣም ድንቅ የመንፈሳዊ ጉዞ ቦታዎች አንዱ” ሲል አወድሶታል።
በተለይም ከመሬት በታች በአንድ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራውና መስቀል ቅርጽ ያለው ቤተ ጊዮርጊስ፣ ጠባብ መተላለፊያዎቹ፣ በውስጡ ካለው ደማቅ ብርሃን፣ የዕጣን ጭስ እና የካህናት ዜማ ጋር ተዳምሮ ልዩ መንፈሳዊ ድባብ እንደሚፈጥር ለተመልካቾቹ አጋርቷል።
ሕይወቱን በአንድ ቦታ ታስሮ ከመኖር ይልቅ አዳዲስ ነገሮችን ለመለማመድ መርጦ ዓለምን እየዞረ የሚገኘው ይህ ድንቅ ተጓዥ፣ በፌስቡክ 2 ሚሊዮን እንዲሁም በዩቲዩብ 1 ሚሊዮን ገደማ ተከታዮች አሉት።
አውሮፓን፣ እስያን፣ አፍሪካንና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን የጎበኘው ዳውድ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ገልጿል። እኛም ሀገራችንን በበጎ ገጽታዋ ለዓለም ስላስተዋወቀልን ከልብ እናመሰግናለን።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: