የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን የተመራውን ልዑክ በቢሯቸው ተቀብለው በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የመከላከያ ትብብር፣ በቀጠናዊ ደኅንነት እና በጋራ የሚከናወኑ የወደፊት የትብብር መስኮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የመከላከያ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፣ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የመከላከያ አጋርነት እና የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ወቅት የትብብር መስኮችን ማስፋት፣ በሶማሊያ አልሸባብን እና አይኤስ አይኤስን ጨምሮ በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገውን ትግል ማጠናከር እንዲሁም ወደፊት ያሉ የትብብር ዕድሎችን መለየት ዋና የውይይቱ አጀንዳዎች እንደነበሩ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ገልጸዋል።
ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለችውን አስተዋፅኦ ያደነቁት ጀነራል መኮንኑ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የአፍሪካ የሎጂስቲክስ እና የኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየምን ማዘጋጀት መቻላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የመከላከያ ትብብር የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ግንኙነት ከጋራ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ባሻገር ዘላቂ እና ዘመናዊ የመከላከያ አቅምን በመገንባት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ ያሉ የደኅንነት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነትም እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር የአፍሪካ የሎጂስቲክስ እና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየምን ማካሄድ መሆኑን ገልጸው፣ ሲምፖዚየሙ ልምድ ለመለዋወጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ ከንግድ ዘርፉ ጋር ትብብርን ለማሳደግና የአፍሪካ የመከላከያ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሀገራት በአንድ መድረክ በማሰባሰብ የጋራ የደኅንነት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን የአመራር ሚና እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክትሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው፣ ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበር እና በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የመከላከያ ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መሳተፋቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: