የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና፣ የኢኮኖሚ ነፃነት እና የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና ነው።
ቀደም ሲል የቀይ ባሕር ባለቤት እና ተጋሪ የነበረችው ሀገራችን፣ በታሪካዊና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶች ምክንያት ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ከባሕር ጠረፍ ርቃ ቆይታለች።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በአፍሪካ ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም እየገነባች የምትገኝ ሀገር ባሕር አልባ ሆና መቀጠሏ ሁለንተናዊ ዕድገቷ ላይ ከባድ ማነቆ ፈጥሯል።
ሀገራችን የወጪ እና ገቢ ንግዷን ከ90 በመቶ በላይ የምታካሂደው በአንድ ብቸኛ የወደብ አማራጭ ላይ ተንጠልጥላ ነው።
ለወደብ ኪራይ እና ለሎጂስቲክስ በየዓመቱ የምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በውጭ ምንዛሬ ክምችቷ ላይ ከፍተኛ ጫና ከማሳደሩም ባሻገር፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን የሕዝብ ዕድገት እና የኢኮኖሚ ፍላጎት ለማስተናገድ እንዲሁም የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ አስተማማኝ እና በራሷ ቁጥጥር ስር ያለ የወደብ አማራጮችን ማግኘት ግድ ይላል።
ከኢኮኖሚው ጫና ባሻገር፣ የአንድ ወጥ ወደብ ጥገኝነት ሀገርን ለከፍተኛ የጂኦፖለቲካዊ ስጋት የሚያጋልጥ አደገኛ አዝማሚያ ነው።
በየጊዜው በሚለዋወጠው የቀይ ባሕር ቀጣና ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም የፖሊሲ ለውጥ ቢከሰት የኢትዮጵያን የንግድ ፍሰት በቀላሉ ከማስተጓጎሉም በላይ ለአጠቃላይ ደኅንነቷ ፈተና መሆኑ አይቀርም።
የኢትዮጵያ ከባሕር ጠረፍ መራቅ የሚፈጥረው የደኅንነት ስጋት ከራሷ አልፎ ለመላው ቀጣና ጭምር የሚተርፍ ነው።
በመሆኑም ይህንን የሕልውና ጥያቄ ለመመለስ ሀገራችን የምትከተለው መንገድ በኃይል እና በጉልበት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰላማዊ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ ነው።
ይህንን ፍላጎት በስምምነት ማሳካት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ለቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: