የአምራች ኢንዱስትሪው የልብ ትርታ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለው ተወዳዳሪነት ነው። ይህ ተወዳዳሪነት ደግሞ በዋጋ፣ በጥራት እና በጊዜ ላይ የተመሠረተ ነው።
ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ከእነዚህ ሦስት ወሳኝ ምሰሶዎች አኳያ ሲመዘን 'የባሕር በር አልባነት' የሚባለው ግዙፍ ማነቆ ጉሮሮውን አንቆ ይዞት ይገኛል።
አንድ ሀገር 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አቅፋ በሰፊ ሀብት ላይ ተቀምጣ፣ ነገር ግን ወደብ አልባ ስትሆን ኢንዱስትሪዎቿ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን ቀርቶ የውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ራሱ እጅግ ፈታኝ ይሆንባቸዋል።
የባሕር በር ጥያቄ የፖለቲካ ትርክት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ፋብሪካ፣ የእያንዳንዱ ሸማች እና የሀገር ኢኮኖሚያዊ ሕልውና ጉዳይ ነው። እናም ወደብ አልባነት በአምራቹ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እጅግ የከፋ ነው።
ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችም ሆኑ ወደ ውጭ የሚላኩ የተጠናቀቁ ምርቶች በከፍተኛ የትራንስፖርት እና የጉምሩክ ውጣ ውረድ ወጪዎች ይደቆሳሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ምርት ቻይና ተመርቶ ናይሮቢ ከሚሸጥበት ዋጋ ይልቅ፣ አዲስ አበባ ሲደርስ ቢያንስ በ30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ያሳያል።
የሎጂስቲክስ ወጪያችን ወደብ ካላቸው ጎረቤቶቻችን ጋር ሲነጻጸር ከ50 እስከ 100 በመቶ ብልጫ አለው። ይህ ማለት አምራቾቻችን ምርታቸውን ለዓለም ገበያ ሲያቀርቡ በወደብ ኪራይ እና በእንግልት ምክንያት ብቻ ዋጋቸው ንሮ፣ በሌሎች ሀገራት ከሚገኙ ተፎካካሪዎቻቸው ጋር እኩል መቆም ያቅታቸዋል ማለት ነው።
በሌላ በኩል የሀገር ገመና እና የንግድ ምሥጢር ከባሕር በር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ጉዳይ እጅግ ጥልቅ በሆነ ምልከታ ሲገልጹት "የባሕር በር አልባነት ገመና አልባነት ነው። የባሕር በር ከሌለህ ገመና አልባ ትሆናለህ" ብለዋል።
ይህ አባባል በኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቅ ትርጉም አለው። የምናስገባው ቴክኖሎጂ፣ የምንልከው ምርት ዓይነት እና መጠን እንዲሁም የዲጂታል መረጃዎቻችን (በውቅያኖስ ውስጥ የሚያልፉ የፋይበር ኦፕቲክስ ኬብሎችን ጨምሮ) በሌሎች ሀገራት እጅ ማለፋቸው የንግድ ምሥጢራችንን በቀላሉ ተጋላጭ ያደርገዋል።
በጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር ውስጥ፣ የንግድ መስመርን ሙሉ በሙሉ በሌሎች ቁጥጥር ሥር ማድረግ አምራቹን ገመና-አልባ ከማድረጉም ባሻገር ስትራቴጂያዊ ሥጋት ነው።
የጊዜ መዘግየት እና የጥራት መጓደልም ሌላው የኢንዱስትሪው ሕመም ነው። የወደብ አልባነት እና የሎጂስቲክስ መጓተት ምርቶች በወቅቱ ለገበያ እንዳይቀርቡ ያደርጋል።
በዚህም ምክንያት የውጭ ገዢዎች በገቡት ውል መሠረት ምርት ባለመድረሱ ኮንትራት ሲሰርዙ፣ ጥራታቸው በቀላሉ የሚበላሹ (perishable) የግብርና እና አግሮ-ኢንዱስትሪ ምርቶች ደግሞ መንገድ ላይ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። ጥራት፣ ጊዜ እና ወጪ የተባሉት የኢንዱስትሪ ስኬት ቀመሮች በወደብ እጦት ምክንያት ሲናጉ፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያዊ ሽግግር ክፉኛ ይደናቀፋል።
ለዚህም የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች ቢሆኑም መንግሥት የደረቅ ወደቦችን (እንደ ሞጆ እና ድሬዳዋ ያሉ)፣ የነጻ ንግድ ቀጣናዎችን፣ የባቡር እና የፈጣን መንገዶችን ማስፋፋቱ እንደ ማስታገሻ የሚወሰድ እጅግ ጠቃሚ እርምጃ ነው። እነዚህ መሠረተ ልማቶች የወጪ ንረቱን በመጠኑ ቢቀንሱትም፣ ዘላቂ መፍትሔ ግን ሊሆኑ አይችሉም።
ከረጅም ጊዜ አኳያ ደግሞ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን የግድ ሲሆን ይህ ጉዳይ የቀጣናውን ሰላም እና የዓለም አቀፍ ንግድ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ጭምር ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያን የመሰለች ግዙፍ አምራች ሀገር ከቀይ ባሕር ርቃ እስከ ወዲያኛው በሩቅ ተመልካችነት ትኖራለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትሥሥር ወደ ኋላ መጎተት ነው።
የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና፣ የኢንዱስትሪ ትንሣኤ እና የብልጽግና መሠረት ነው። ኢንዱስትሪዎቻችንም በዓለም መድረክ መወዳደር የሚችሉት፣ አምራቹ በትርፍ አቅሙን ማሳደግ የሚችለው፣ እንዲሁም ዜጋው ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችለው የሎጂስቲክስ ማነቆው በዘላቂነት ሲፈታ ነው።
በመሆኑም የባሕር በር ጥያቄ የእያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት የኑሮ ትግል አካል መሆኑን ተገንዝበን፣ ይህን ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ለመጠገን የሚደረገውን ጥረት መደገፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: