Search

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ25 ዓመታት ሀገር አቀፍ ማስተር ፕላን ጥናት ይፋ አደረገ

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 41

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል አቅርቦት ሥርዓት ወደ ዘመናዊና ዲጂታል አሠራር ለማሸጋገር ያስጠናውን 25 ዓመታት ሀገር አቀፍ ማስተር ፕላን ጥናት ይፋ ማድረጊያ ዎርክሾፕ በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

ማስተር ፕላኑ የኃይል አቅርቦት ሥርዓታችንን ወደ አዲስ የዲጂታል ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ገልጸዋል።

የማስተር ፕላን ጥናቱ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ፣ የኔትወርክ ችግሮችን በተቀናጀ ሁኔታ ለመፍታት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለመዘርጋት የሚያስችል ስለመሆኑም ተመላክቷል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው ይህ የማስተር ፕላን ጥናት የተቋሙን አሠራር ወደ አዲስ ዲጂታል ምዕራፍ የሚያሸጋግርና በቀጣይ ሩብ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ አስተማማኝና ጥራት ያለው የኃይል አቅርቦት ለማረጋገጥ መሠረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በስኬት እንዲተገበር ከባለድርሻ አካላትና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የሚደረገው ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑን ስለመሆኑም ተነስቷል።

በተደረገው ጥናት መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 100 መጋቢ መስመሮች፣ 183 ሰብስቴሽኖች እና 79 ሺህ ኪሎ ሜትር ነባር መካከለኛ መስመሮች ዳሰሳ መደረጉ ይፋ ሆኗል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እና ባለድርሻ ድርጅቶች የተሰበሰቡ ግብዓቶች ተካትተውበት ማስተር ፕላኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: