በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊ ትብብር መስክ ያለው የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ይበልጥ ወደ ስትራቴጂያዊ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በጋራ ያዘጋጁት የ2026 የአፍሪካ ኮሙኒኬሽን እና ሎጂስቲክስ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
ኢትዮጵያ ይህን ታላቅ አህጉራዊ መድረክ እንድታስተናግድ መመረጧ ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላትን አስተዋፅኦ፣ በልማት ያስመዘገበችውን ውጤት እና አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ ከፍተኛ አቅም ያላት መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ከ40 በላይ የአፍሪካ ሀገራት እና 25 የአሜሪካ የኢንዱስትሪ አጋሮች የተሳተፉበት ይህ መድረክ የአፍሪካን የደኅንነት አቅም በተግባራዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው።
አምባሳደር ማሲንጋ በዚሁ ጊዜ እንዳብራሩት አጋርነት መፈክር ሳይሆን በመተማመን እና በግልጽነት የሚገነባ አቅም ሲሆን፣ የሎጂስቲክስ እና የመገናኛ ሥርዓት ደግሞ ለወታደራዊ ተልዕኮ ውጤታማነት፣ ለተፈጥሮ አደጋ ምላሽ፣ ለድንበር ጥበቃ እንዲሁም ለሰላም ማስከበር ቁልፍ መሠረት ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ በአመራሯ እና በስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዋ የቀጣናውን እና የአህጉሩን አቅጣጫ ከቀረጹ ሀገራት መካከል መሆኗን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
አሜሪካ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በእኩል አጋርነት ለመሥራት፣ የአፍሪካን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለመደገፍ እና ተቋማዊ አቅማቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
በአህጉሩ የሚታዩ እንደ ሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ ዝውውር እና የሳይበር ስጋቶችን በጋራ ለመቀልበስ ይህ ሲምፖዚየም ዘላቂ የትብብር መዋቅር ለመገንባት ምቹ ዕድል እንደሚፈጥርም በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: