Search

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ አፈጻጸም እጅግ ውጤታማ ነው፦ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ

ሰኞ ሐምሌ 20, 2018 34

የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት 2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና የኢኮኖሚና የፋይናንስ አፈጻጸማቸውን በመገምገም፣ 2019 ዕቅዶችና የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ 2018 የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም እጅግ ውጤታማ እንደነበር ገልጸው፤ በተለይም የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግና ከልማት አጋሮች ጋር የሚደረገውን ትብብር በማጠናከር በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ አበዳሪ አካላት ጋር በተደረገው የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት መሠረት ክፍያ መፈጸም የተጀመረበት ስኬታማ ዓመት እንደነበር ጠቁመዋል።

2019 በጀት ዓመትን በተመለከተም የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጠናክሮ በመቀጠል፤ የጸደቀውን በጀት በተሟላ መልኩ ማሳካት እና የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ሆረታ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጎን ለጎን የተጀመሩ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች በዘንድሮው በጀት ዓመትም ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሚመለከታቸው አመራሮች ማብራሪያ ተሰጥቶ ውይይቱ ተጠናቋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: