የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ የያዙ ዜጎች ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በድምፅ ሰጪነት በሚሳተፍበት በዚህ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን የሰጡን የሐዋሳ ከተማዋ ነዋሪዎች አመልክተዋል።
ነዋሪዎቹ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር እና በሌሎችም ጉዳዮች ለሀገር ዕድገት የተሻለ ይሠራል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ በመምረጥ የዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ አካል ለመሆን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

አቶ በለጠ ታልጋ እና ወይዘሮ ጽዮን ተስፋዬ እንደተናገሩት የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ እንዲሰፍን ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ማካሄድ ተገቢ ነው።
በየአምስት ዓመቱ የሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝብ በቀጥታ ተሳትፎ "ይሆነኛል፣ ይበጀኛል" ለሚለው ፓርቲ ድምፁን የሚሰጥበት በመሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልምምድ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።
የአንድ ሰው ድምፅ በአጠቃላይ በምርጫው ውጤት ላይ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ካርድ የያዙ ዜጎች ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሚካኤል ገዙ