የኢትዮጵያ የወደፊት የአምስት ዓመታት የፖለቲካ እና የልማት ምዕራፍ የሚወሰንበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በከፍተኛ መነሣሣት ድምፃቸውን ሲሰጡ ውለው በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት መራጮች፣ ረጅም ሰልፎችን በመያዝ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ የሆነውን የዜግነት ግዴታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተወጥተዋል።
በምርጫው ሂደት ላይ ለመሳተፍ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ምዝገባ ማካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን የድምፅ መስጠት ሂደቱ ላይም ሕዝቡ ያሳየው ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ እና ታሪካዊ ነበር።
በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡ ዜጎች “የእኔ አንድ ድምፅ ለሀገር ግንባታ፣ ለዘላቂ ሰላም እና ለሉዓላዊነት መከበር ወሳኝ ሚና አለው” በሚል እምነት በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለምንም ሳይበገሩ መርጠዋል።
መራጮቹ የሀገር ጉዳይ እንደሚቀድም በማሳየት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት አስመስክረዋል።
በዚህ ምርጫ አሸናፊዋ ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት፤ “ኢትዮጵያ አትችልም” እያሉ ሲያሟርቱባት የነበሩትን አካላት በሕዝቦቿ ፅናት ችላ አሳይታቸዋለች፤ አሳፍራቸዋለች።
ይህ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ እና በቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገርን በብቃት የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሰየም የተደረገ ወሳኝ እርምጃ ነው።
የምርጫ ቦርድ ይፋዊ ውጤት እስከሚያወጣ ድረስ ሕዝቡ ያሳየውን የሠለጠነ እና ሰላማዊ ባህልን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል።