Search

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናውን አቀረበ

ማክሰኞ ግንቦት 25, 2018 127

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባሰራጨው መረጃ እንዳስታወቀው፣ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ እና ውጤታማ የሆነ ስትራቴጂክ አመራር ሰጥተዋል።

መላው አባልም የተሰጠውን ስምሪት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ቀን ከሌት በማከናወን ምርጫ ለኢትዮጵያ ሰላም እና ደኅንነት የሚያበረክተውን ጉልህ ሚና ተወጥቷል።

ምርጫ ለሀገራዊ ደኅንነት እና ሰላም የሚያበረክተውን ፋይዳ ከተቋማዊ ተልዕኮ ጋር አስተሳስራችሁ በከፍተኛ ብቃት የመራችሁ እና የፈጸማችሁ አመራሮችና አባላት በሙሉ ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያበረከታችሁት አስተዋፅኦ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ከፍታ ማሳያ ሆኖ ስለሚጠቀስ እናመሰግናለን ያለው መረጃው፣ የኢትዮጵያን ደኅንነት ማረጋገጥ! በሚል አንድ ሀገራዊ ዓላማ ሥር በመሰባሰብ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከተቋሙ ጋር በትብብር እና በአጋርነት ተልዕኳቸውን የተወጡ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ እና የመረጃ አካላትም የላቀ ምስናጋና እንደሚገባቸው ጠቅሷል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለምርጫው ስኬት ያሳየው ቁርጠኝነትና ብስለት እንዲሁም እስከ እኩለ ሌሊት ድምፅ በመስጠት ያሳየው ትዕግስትና ፅናት ለሀገራዊ ደኅንነቱ ደጀን መሆኑን ስለሚያረጋግጥ ክብርና ምስጋና እንደሚገባው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከቅድመ ምርጫ ወቅት ጀምሮ ከተቋማዊ ተልዕኮ የመነጩ የመረጃ፣ የደኅንነት እና የሥነ-ልቦና ጦርነት ሥምሪቶችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ሲያከናውን መቆየቱን ያስታወሰው መረጃው፤ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የሚያግዙ አስቻይ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ፣ በማሟላት እና በመታጠቅ ለምርጫው ስኬታማነት ጥቅም ላይ ማዋሉን ጠቅሷል።

ተቋሙ ባዘጋጀው 2ኛው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፈረስ ከሀገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ የደኅንነት አዝማሚያዎች ላይ ግምገማ በማካሄድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመረጃ፣ በደኅንነት፣ በሥነ-ልቦና ጦርነት እና በፀጥታ ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት መካሄዱን ማረጋገጡን አስታውሷል። 

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ደኅንነት ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ለአባላት የምርጫ ደኅንነትን በሚመለከት ስልጠና በመስጠት ዝግጁነታቸውን በማሳደግ ሀገር አቀፍ ስምሪት ተደርጎ እንደነበርና ውጤታማ አፈጻጸም ማሳየታቸውን መረጃው ገልጿል።

ተቋሙ ሰላማዊ የድኅረ ምርጫ ድባብ እንዲሰፍን በመላ ሀገሪቱ የመረጃና ደኅንነት ስምሪቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።