ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም ያቀደችውን የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚባክን ጊዜ እንደሌለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም የተገነባውን የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ምረቃ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ያለ ምንም ስጋት፣ ብርዱን እና ዝናቡን ተቋቁሞ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ድምፁን መስጠቱ፤ አስደማሚ እና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም አመለክተዋል።
“ለምርጫው ድምፅ በሰጠን ማግስት በቀጥታ ወደ ሥራ ገብተናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ መላው የመንግሥት አመራር በፌዴራል እና በክልል ደረጃ በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ መመለሱን አስታውቀዋል።
ለዚህም ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የ10.2 በመቶ ዕድገት ለማረጋገጥ የያዘችውን ግብ ለማሳካት መሆኑን አስረድተዋል።
በጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜ አንድ ወር ከአምስት ቀን ብቻ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ሰኔ 30 የበጀት ሥራው የሚጠናቀቅበት በመሆኑ፣ ያቀድነውን ዕድገት ለማሳካት የሚባክን ጊዜ የለንም፤ በመሆኑም በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አለብን" ብለዋል።
ዛሬ በይፋ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት የሆነው ፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ቁስቋም ጀምሮ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ድረስ 9.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የሸገር ፕሮጀክት አካል ነው።
በላሉ ኢታላ
