በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። ምክር ቤቱ የአማራ ሕዝብ ለዴሞክራሲ በከፈለው መሥዋዕትነት ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን አስታውቋል።
23 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኙበት ይህ ምክር ቤት፣ ምርጫው በነፃነት እና ያለምንም ተጽዕኖ የተካሄደ እና ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና ለምርጫው ስኬት ድርሻ ለነበራቸው አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርቧል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀመንበር እና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ እንደገለጹት፣ ምርጫው ዜጎች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡበት እና ለሀገራችን የዴሞክራሲ ልምምድ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ታሪካዊ ክስተት ነው።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተዓማኒ ሆኖ መከወኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ በዚህም ሀገራችን ኢትዮጵያ አሸንፋለች ብለዋል።
ሕዝቡ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ ወጥቶ መሳተፉን እና "ይሆነኛል፤ ይበጀኛል" የሚለውን መምረጡን አቶ ተስፋሁን ጠቁመዋል። ምርጫውን ለማደናቀፍ ከውስጥም ከውጭም ጥረቶች ቢደረጉም፣ በጀግናው የፀጥታ ሠራዊት ማክሸፍ በመቻሉ ለሁሉም የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድኅረ-ምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በፀጋ ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ተስፋሁን አሳስበዋል።
በተስፋሁን ደስታ