የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ትናንት የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ምርጫውን ሊያደናቅፍ እና ሰላሙን ሊያናጋ የሚችል ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር በስኬት መጠናቀቁን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ የሕዝብን ውሳኔ በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ መቆየቱን ገልጿል።
በድምፅ መስጫው ዕለትም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን በነፃነት እና በሰላም ከሰጠ በኋላ ወደ ቤቱ መመለሱ በመግለጫው ተመልክቷል።
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫውን ሕግ እና ሥርዓት ጠብቆ በመሥራት በኩል ጥቃቅን የሥራ ክፍተቶች ታይተው የነበረ ቢሆንም፣ ችግሮቹን በአስቸኳይ ለመቅረፍ እና መፍትሔ ለመስጠት በተደረገ የተቀናጀ ጥረት ሒደቱ ሳይስተጓጎል ሊቀጥል ችሏል።
ይህ የምርጫ ሒደት በክልሉ እያደገ ለመጣው እና ለተረጋጋው የፖለቲካ ባህል ትልቅ ማሳያ መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ጠቅሷል።
ምርጫው በስኬት እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የክልሉ ሕዝቦች ለፀጥታ አካላት እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርቧል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በምርጫ ማስፈጸም ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በውይይት እና በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የተቋቋመ የጋራ መድረክ ነው።
በአሚር ጌቱ