Search

የጋራ ምክር ቤቱ የሕዝቡን ውሳኔ እና ድምፅ ያከብራል፦ የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ማክሰኞ ግንቦት 25, 2018 61

የሐረሪ ክልል የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ የታዩ አዎንታዊ ጅምሮችን ይበልጥ በማጠናከር የምርጫውን ሰላማዊነት፣ ዲሞክራሲያዊነት፣ ነፃና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነቱን ማጠናከር እንደሚገባ አንስቷል።

በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የቀረቡ ቅሬታዎችን፣ የአፈጻጸም ክፍተቶችን እና ተግዳሮቶችን በጥንቃቄ በምርጫ ዴስክ በኩል ለመፍታት ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሰው ምክር ቤቱ፣ በአሁኑ ወቅትም ቅሬታዎችን በሕጋዊ እና በተቋማዊ አግባብ ለመፍታት ተገቢው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን ውሳኔ እና ድምፅ እንዲያከብሩ እና ደጋፊዎቻቸውንም ወደ ሰላም፣ መከባበር እና ሕጋዊ አሠራር እንዲመሩ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት በውይይትና በሕግ ማዕቀፍ ብቻ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

የምርጫው ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ መሠረት ተረጋግጦ እስከሚጠናቀቅና ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትዕግሥት እና በኃላፊነት ስሜት መጠባበቅ እንዳለባቸውም ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ከምርጫ በኋላ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር እና የመግባባት ባህል ይበልጥ እንዲጠናከር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ምክር ቤቱ አረጋግጧል።

የጋራ ምክር ቤቱ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ በንቃት ለተሳተፉ ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ አስተዳደር አካላት፣ የፀጥታ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የሚዲያ ተቋማት ለተወጡት ሀገራዊ ከፍ ያለ ክብር እንደሚሰጥ በመግለጫው አስታውቋል።

በቴዎድሮስ ታደሰ