የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅቶችን በጽናት የመሻገር፣ የሀገሩን ሉዓላዊነት እና አንድነት የማስጠበቅ ታላቅ ጥበብ እንዲሁም የማንነት አሻራ ባለቤት ነው፡፡
ትናንት በታሪክ አደባባዮች በጀግንነት የታየው ይህ የሀገር ፍቅር ተጋድሎ፣ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ሕዝቡ ለሀገሩ ያለውን የማይናወጥ ታማኝነት እና ጽናት ዳግም ለመላው ዓለም ያሳየበት ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ በወርቅ ቀለም ተመዝግቧል፡፡
በተለይም በዚህ ታሪካዊ ሂደት ላይ ማኅበረሰቡ የዜግነት ድርሻውን ለመወጣትና ድምጹን ለመስጠት ያሳየው ወደር የለሽ ቁርጠኝነት እጅግ የሚያስደንቅና በኩራት የሚነሳ ነው፡፡
ማንኛውም ዓይነት አስገዳጅ ሁኔታዎች፣ ጊዜያዊ ፈተናዎች እና ማነቆዎች ሳይገድቡት በማለዳው ብርድ እና በቀትሩ ፀሐይ ሳይበገር፣ ረጅም ሰዓታትን በትዕግሥት እና በሰላማዊ መንገድ በመጠበቅ ታላቅ ኃላፊነቱን በስኬት ተወጥቷል፡፡
ሕዝቡ ያሳየው ይህ ተአምራዊ ጽናት በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ የውጭ ጫናዎችን በቁርጠኝነት ለመቋቋምና የውስጥ ተግዳሮቶችን በአብሮነት ጥንካሬ ለማለፍ ያለውን ጥልቅ ፍላጎት በግልጽ ያነጸባረቀበት ነው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ልዩነቶቹን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መወሰኑ፣ የሠለጠነ ማኅበረሰብ እና የላቀች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ያለውን ጽኑ ራዕይ በተግባር ያሳየበት ደማቅ ክስተት ሆኗል፡፡
ይህ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን በራሱ ለመወሰን ያደረገው ታላቅ ተጋድሎ፣ የሕዝቡን የላቀ የፖለቲካ ብስለት እና ለሀገር ህልውና ያለውን ቀናኢነት በተግባር ያረጋገጠ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ታላቅ ስኬት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያን ሕዝብ ታላቅነት በታላቅ አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት "የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂም ተአምረኛም ሕዝብ ነው። ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅና ሊገመግም የሚችል ማን ነው? የዳበረ ባህል፣ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ሕዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም አሳይቷል" በማለት የሕዝቡን የጸና ጥንካሬ አውስተዋል፡፡
ይህ መልዕክት እንደሚያመላክተው ምንም ዓይነት ጊዜያዊ ማዕበል እና ፈተና የኢትዮጵያን የነገ ብሩህ ተስፋ ሊያጨልም አይችልም፡፡
የሕዝቡ አንጸባራቂ የሀገር ፍቅር ምንጊዜም የጸና መሆኑን ይህ ታሪካዊ ክስተት ትልቅ ማረጋገጫ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብር፣ ሰላም እና ዕድገት ሲሉ በጽናት ቆመው ለመጻኢ ጊዜ የሚሆን ብሩህ ውሳኔያቸውን በሉዓላዊ እጃቸው አሳልፈዋል፡፡
አሁን ግን ቀሪው ታላቅ ኃላፊነት የተመራጮች ትከሻ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ሕዝቡ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ የሀገር አደራ የሰጣቸው ተመራጮች፣ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ሰላም፣ ክብር እና ልማት ቀን ከሌት በታማኝነት መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በለሚ ታደሰ