7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን የአፋር ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገልጿል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በንቃት ሲከታተል እንደነበር አስታውሷል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እና የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር ሐንፍሬ አሊሚራህ፣ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በየምርጫ ጣቢያዎቹ እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ እንደነበር እና ሂደቱም ሰላማዊ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጫው ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ በሰላም መከናወኑን ገልጸው፣ አልፎ አልፎ ያጋጠሙ ጥቃቅን ችግሮችም ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር መፈታታቸውን ጠቁመዋል።
የአፋር ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል እና የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ መሐመድ ዳውድ በበኩላቸው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች በአሳታፊነቱ እና በዲሞክራሲያዊነቱ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ነው የገለጹት።
በባዬ ሙላት