Search

የመደመር ዲፕሎማሲን የስኬት ሚስጥር ያውቁታል ?

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 29

የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተለዋወጠ፣ የአንድ ዋልታ የበላይነት እያከተመ ወደ ባለብዙ ዋልታ (multipolar) ሥርዓት እየተሸጋገረ ባለበት በአሁኑ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት አንስቶ አዲስ እና ዘመናዊ የመደመር ዲፕሎማሲን በመከተል ላይ ትገኛለች። እርስዎ ስለመደመር ዲፕሎማሲ ምን ያህል ያውቃሉ?

ዛሬ ጥቂት ልንገርዎት!! ይህ አዲሱ የመደመር የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ዕይታ፣ በፈጣን የዓለም የለውጥ ዑደት ውስጥ ከሕልውና ማረጋገጥ ባሻገር የሀገርን ዘላቂ ልዕልና ማሳካትን ግቡ ያደረገ ምሉዕ እና ሚዛናዊ የእይታ ማዕቀፍን የተላበሰ ነው።

ከለውጡ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀዳሚ መነሻውን የሀገር ውስጥ ተጋላጭነት አድርጎ የሚነሳ፣ የዓለምን ሁኔታ በጥርጣሬ፣ በስጋት እና በሴራ መነጽር የሚመለከት የእውናዊነት (Realism) አቅጣጫን በዋናነት ያዘነበለ ነበር። አዲሱ የመደመር ዲፕሎማሲ ግን ይህንን የተቸከለ አቋም በመቀየር ከርዕዮተ ዓለም እስረኛነት እና ከአስተሳሰብ ተቸካይነት የተላቀቀ ተራማጅ ዕይታን አምጥቷል።

May be an image of one or more people, beard, suit and dais

የመደመር ዕይታ እውናዊነትን እና ሊበራሊዝምን (Liberalism) በማስታረቅ፣ በፉክክር እና በትብብር መካከል ያለውን ሚዛን የጠበቀ የውጭ ግንኙነት ፍልስፍናን ያራምዳል። አገራት በውጭ ግንኙነታቸው ፉክክርን ብቻ ሳይሆን ትብብርን ማዕከል አድርገው፣ በሚዛን መዛባት የሚፈጠርን የብቸኝነት ጉድለት በመሙላት በጋራ ሊያድጉ እንደሚችሉ ያምናል። ይህ አካሄድ በዋልታ ረገጥ ድምዳሜዎች ከመታሰር ይልቅ፣ ተለዋዋጭ ለሆኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ተላማጅ እና ተለማጭ (adaptable and flexible) የመሆንን ትልቅ አቅም ሰጥቶታል።

የመደመር ዲፕሎማሲ መለያ ባህሪያት ዘርፈ ብዙ ሲሆኑ፣ ዋነኛ መለያው ብሔራዊ ጥቅምን ቋሚና ተበይኖ ያለቀ ነገር አድርጎ አለመውሰዱ ነው። ብሔራዊ ጥቅም በእሴት ላይ በተመሠረተ ምክንያታዊ ንግግር፣ በጋራ መግባባት፣ እና የዜጎችን ክብር ማዕከል አድርጎ የሚዳብር መሆኑን ይቀበላል።

May be an image of dais and text

ወዳጅን ማብዛት እና አጋርነትን ማጎልበት፡ አዲሱ ዲፕሎማሲ የቅርብም ሆነ የሩቅ አገራትን በቋሚ ባላንጣነት ወይም ጠላትነት ከመፈረጅ ይቆጠባል። ይልቁንም ዲፕሎማሲን አጋርን ማብዛት፣ ችግሮችን ለመፍታት ቀዳሚውን ስፍራ ግንኙነትን ለማደስ መስጠት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ትብብር መፍጠርን ዓላማው አድርጓል።

May be an image of one or more people, dais and text that says 'G20 SOUTH AFRICA SOUTHAFRICA2025 2025'

የመልካም ጉርብትና እና የቀጠናዊ ትስስር ቅድሚያ፡ በቀጠናው አገራት መካከል የጥርጣሬ ድባብን በማስወገድ፣ ኢትዮጵያ ለቀጠናው የዴሞክራሲ፣ የሰላም እና የፈጣን ዕድገት ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችል ዕይታን አምጥቷል። የኢነርጂ፣ የንግድ እና የመሰረተ ልማት ትስስርን በማስፋት ቀጠናዊ ውህደትን እውን ለማድረግ ይተጋል።

No photo description available.

አዲስ የኢኮኖሚ እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፡ ዲፕሎማሲን ከእርዳታ እና ብድር ጥገኝነት አዙሪት በማውጣት ዘላቂ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ ገበያ ፍለጋ እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ላይ ትኩረት አድርጓል። በተጨማሪም፣ ዜጋ ተኮር በመሆን በውጭ የሚኖሩ ዜጎች መብትና ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ እንዲሁም በሀገር የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሰፊ ምህዳር ፈጥሯል። የባሕር በር ጥያቄንም ቢሆን በሰጥቶ-መቀበል መርህ፣ በሰላማዊ እና በህጋዊ መንገድ ለማሳካት የሚሰራው ይኸው የዲፕሎማሲ መርህ ነው።

በአጠቃላይ፣ አዲሱ የመደመር ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን ከትናንት የውስጥ ተጋላጭነት አዙሪት በማውጣት፤ ዛሬንና ነገን ባስተሳሰረ፣ የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በሚመጥን እና የሀገራችንን ብሔራዊ ክብርና ሉዓላዊነት በከፍታ ላይ በሚያጸና ዘመናዊ የእይታ ማዕቀፍ እየተመራ ይገኛል። ይህ የጠራ፣ ዕዳን ወደ ምንዳ፣ ግንኙነትን ወደ ተጠቃሚነት የሚቀይር ዲፕሎማሲ ነው ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ተደማጭ እና የጋራ ብልፅግና አንከር አገር እንድትሆን እያደረጋት የሚገኘው።