ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ “የሐዋሳን ብርሃን፣ የሕዝቡን ፍቅር እና ታሪካዊ ማንነቱን በቅዳሜ እና እሑድ እየመጣችሁ እንድትጋሩ፣ የእኛን ደስታ ተካፈሉ" ሲሉ ከሐዋሳ ግብዣ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ65ኛው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምሥረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ስለ ሐዋሳ ሲገልጹ፣ “ሐዋሳ የኢትዮጵያ ሁነኛ ራዕዮች የሚበሠሩበት፣ ቄጤላ በውስጥ የሸሸግነውን፣ በቤት የመከርነውን፣ በዝማሬ የምንገልጽበት፣ ይህ ቦታ በተደጋጋሚ ያለምነውን የተናገርንበትን ስናሳካም በጋራ ድል ያበሰርንበት ቦታ ስለሆነ፤ ለመላው የሲዳማ ሕዝብ በተለይም ቄጤላን በውብ መንገድ ላቆዩልን አባቶች የከበረ ምስጋናዬን ላቀርብ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ በዚሁ ቦታ አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ እናደርጋታለን ባልነው መሠረት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በርካታ ከተሞች አበባ ሆነው፣ ሐዋሳ ደግሞ ብርሃን ሆና ስላየናት የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሐዋሳ ተሞሽራለች፤ ቅዳሜ እና እሁድ ምን ታደርጋላችሁ? ኑ እና አስተናግዳችሁ እያለች ስለሆነ በአዲስ አበባ ያላችሁ ሰዎች የሐዋሳን ብርሃን፣ የሕዝቡን ፍቅር እንዲሁም ታሪካዊ ማንነቱን በቅዳሜና እሁድ እየመጣችሁ እንድትጋሩ፣ የእኛን ደስታ እንድትካፈሉ ሲሉ ግብዣ አቀርበዋል።
የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ምርጥ ከንቲባ ማግኘታቸውን ጠቁመው፣ እንደዚህ ያለው ዕድል ሁልጊዜ ስለማይሳካ ከንቲባውን በመደገፍ፣ ውቢቷን ሐዋሳ ዳግም በመሥራት፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊመጣባት የሚጓጓት ዓለም አቀፍ ከተማ እንድትሆን ባላችሁ አቅም ሁሉ ከከንቲው፣ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጎን በመቆም፣ ሐዋሳን ዳግም እንድንገነባ በታላቅ ትህትና አደራ ብለዋል።
ሐዋሳ ባሳየችው ለውጥ ሳንረካ፣ በዚህ ሳንቆም ቀን ከሌት በመሥራት ሐዋሳን ብዙ አፍሪካውያን መጥተው የሚጎበኟት፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት፣ እንዲህ ያለው ትልቅ በዓል የሚከናወንባት መዲና እንድትሆን መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ በመሆን እቺን የፍቅር ከተማ እንድንገነባ ሲሉ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ፍቅር አክብሮታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ በአዲስ ታሪክ እና በታላቅ ስኬት እንደምንገናኝ ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።